
ወልድያ: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳደር እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አዛዦች፣ የወረዳ የጸጥታ መዋቅር አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አበጋሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በእርቅ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
በተሠራው ሥራም በሀብሩ ወረዳ የኩልባይኔ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩ 15 ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።
የኩልባይኔ ቀበሌ ሊቀመንበር የነበሩት አህመድ ሰኢድ በተሳሳተ መረጃ እና በመደናገር ወደ ጽንፈኛው ቡድን ተቀላቅለው እንደነበር ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ቡድኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተሳሳተ አቅጣጫ እንደተከተሉ በመረዳት የሰላምን አማራጭ መቀበላቸውን አስረድተዋል።
መንግሥት ወንጀለኛን መቅጣት ሲገባው ይቅርታ ማድረጉ ለሰላም ያለውን ፍላጎት እና ለሕዝቡ ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ስለመኾኑ ማረጋገጫ ነው ብለዋል። ላጠፉትም ጥፋት ኅብረተሰቡን ይቅርታ መጠየቃቸውን ነው የተናገሩት።
ሌሎች በመርሐ ግብሩ ሃሳባቸውን የገለጹ በሰላም የገቡ ወንድሞች ዓላማውን ሳይረዱ እና በጭፍን ተወናብደው እንደገቡ ነው የገለጹት።
በቆይታቸው ቡድኑ ውንብድና እና ዝርፊያ ላይ የተሰማራ መኾኑን በማረጋገጣቸው በሰላም ወደ ሕዝባቸው ለመቀላቀል እንደመጡ ነው ያስረዱት።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ ሼህ ሙሄ ሀሰን መንግሥት ልጆቹን በይቅርታ ተቀብሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ጫካ የገቡ ሌሎች ልጆችም ቤተሰብ ያላቸው በመኾኑ ከያዙት የጥፋት ጎዳና ተመልሰው ቤተሰባቸውን እና ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ሸምግሎ ለመመለስ ጥረቱ እንዲቀጥልም ነው ያሳሰቡት።
የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ከድር ሙስጠፋ ማኅራዊ እና ሃይማኖታዊ እሴትን የሚጥስ ትውልድ ተፈጥሯል ብለዋል። የሃይማኖት አባትን፣ ሽማግሌን፣ አባትን እና እናትን ማክበር ተሸርሽሯል ነው ያሉት።
የአካባቢው ማኅበረሰብ እና የሃይማኖት አባቶች የሕዝብን እሴት ትውልዱ ላይ የማስረጽ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የአካባቢውን ችግር በራስ መፍታት ይገባል ብለዋል። ለዚህም የሕዝቡ ትብብር ቁልፍ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት። በመኾኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ልጆቻቸውን በመምከር እንዲመለሱ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መለከላከያ ሠራዊት ምክትል አዛዥ ለኦኘሬሽናል ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ “ጫካ ያሉት ልጆች የእናንተ ልጆች ብቻ ሳይኾኑ የእኛም ወንድሞች ናቸው ለችግር እንዲጋለጡ አንፈልግም” ሲሉ ለማኅበረሰቡ አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ መከላከያ የኅብረተሰቡን ደኅንነት መጠበቅ ቅድሚ የሚሰጠው ኀላፊነቱ ስለኾነ ልጆቹ ከውንብድና ካልወጡ ሕግ የማስከበር ሥራው ይቀጥላል ነው ያሉት።
አሁን በሰላም የተቀላቀሉ ወንድሞችን ደኅንነት እንጠብቃለን ያሉት ሜጄር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥ አርጌ ወደፊትም የተሳሳቱ ልጆችን መክሮ የመመለስ ሥራ ኅብረተሰቡ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
