
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ለ2012/2013 የመኸር ምርት ዘመን 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በመደበኛ እና ከ900 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በአዲስ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዘንድሮው የመኸር ምርትም ከ145 ሚሊዮን 787 ሺህ 514 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ቢሮው ተናግሯል፡፡
ወቅታዊው የዓለማችን የጤና ስጋት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ተከትሎ ዓለም ፈታኝ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ሊገጥማት እንደሚችል የበርካቶች ስጋት ነው፡፡ ምንም እንኳን ድንገት በተፈጠረው የጤና ችግር ምክንያት ሀገራት ድንበሮቻቸውን በፍጥነት መዝጋታቸው የአገልግሎት ዘርፉ እና ኢንዱስትሪው ቀድመው ቢጎዱም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ከጉዳት እንደማያመልጥ ዓለም አቀፋዊ ትንበያዎች ያመላክታሉ፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋሁን መንግሥቴ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በመደበኛ ካለው 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተጨማሪ ከ900 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለመኸር እርሻ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ይህም በአልሚዎች የተያዙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን እንደሚጨምር ምክትል ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጓጉዞ እየገባ መሆኑንም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡ ከ800 ሺህ በላይ ኩንታል የከረመ የአፈር ማዳበሪያ በመኖሩ በክልሉ እጥረት እንደማይኖርም ተናግረዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችላቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ወደ አርሶ አደሩ ቀዬ እንዳይገባ በጥምረት እየተሠራ እንደሆነም ቢሮው አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ከፍተኛ የሆነ የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩን አርሶ አደሮች መግለጻቸውንና ቢሮውም ችግሩ መኖሩን ዕውቅና እንዳለው ዘግበን ነበር፡፡ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሔ ርምጃዎችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማድረስ መረጃዎችን አብመድ እያጣራ ነው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
