
ደብረ ታቦር: ኅዳር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር በራሳቸው ተነሳሽነት በዶሮ ሃብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩት አባ ዜና ስላሴ መንግሱቱ እና ዲያቆን ተክለማርያም ወርቁ በዘርፉ ከ480 ያላነሱ ዶሮዎችን በመያዝ በቀን እስከ 430 እንቁላል በማምረት ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሥራ ማጣት ቁጭት ፈጥሮባቸው ወደዚህ የሥራ መስክ እንደ ተሰማሩም አስረድተዋል። ካላቸው የመነሻ ሃብት በተጨማሪ ከባንክ ብድር ተመቻችቶላቸው ሥራውን እንደጀመሩም ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተበደሩትን ብደር መልሰው የራሳችውን ካፒታል ማስቀመጥ እንደቻሉም አስገንዝበዋል። ሥራ ሲጀምሩ ስለ ደሮዎቹ የጤና እንክብካቤ የነበራቸው ግንዛቤ አናሳ ስለነበር የደሮዎቹ ጤንነት አደጋ ላይ እንደነበርም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው የዶሮዎቹን ጤንነት በጥሩ ሁኔታ እየተከታተሉ እንዳለ አንስተዋል። ወጣቱ ሥራ ሳይንቅ እኛን ምሳሌ አድርጎ መሥራት አለበት ሲሉም መክረዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የእንሰሳት ጤና አገልግሎት ማስፋፊያ ባለሙያ ጋሸው መንግሥቱ በደሮ ልማት ላይ አስፈላጊው ሕክምና እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል።
ደሮ ለማርባት ትልቁ ሥራ ሥነ ምኅዳሩን መጠበቅ እና ዶሮዎችን ከበሽታ በመከላከል ምግብ በሚገባ ማቅረብ እንደኾነ አቶ ጋሻው አስረድተዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ በስፋት የስጋ ደሮ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል። ወደ ዘርፉ ለሚገቡት ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ የባለሙያ ክትትል እና ድጋፍ እየተሰጠ መኾኑንም የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እንሰሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ንጉሴ መርሶ ተናግረዋል።
ተወካይ ኀላፊው በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ሸድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ካሉት በተጨማሪ በግለሰቦች ደረጃም እየሠሩ ላሉት ክትትል እየተደረገ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
በክትትላቸውም ቅድሚያ ለእንቁላል ጣይ ዶሮዎች ክትባት እንደ ሚሰጡ ነው የተናገሩት። በዚህ የሥራ ዘርፍ ለመሰማራት ቀድሞ በራስ ከመጀር ይልቅ ባለሙያን ማማከር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
