
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአሜሪካ እና ፈረንሳይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) አባላት እና ደጋፊዎች ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አልማ አስታውቋል፡፡ አልማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚኖሩ አባላቱን እና ደጋፊዎቹን በማስተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዓለማየሁ ሞገስ ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ዛሬ በውጭ ከሚኖሩ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ በተገኘ ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተገዛ የሕክምና ቁሳቁስ ለክልሉ የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል እና ለጤና ቢሮ እንደሚያስረክብም አስታውቀዋል፡፡
“11 ሺህ 500 መደበኛ የሆኑ እና ለማንኛውም ሰው የሚሆኑ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ፣ 300 ለሕክምና ባለሙያዎች ብቻ የሚያገለግሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎች ከነመለዋወጫቸው ተገዝተው ገብተዋል” ብለዋል አቶ ዓለማየሁ፡፡
የሕክምና ቁሳቁሶቹ ለመተማ፣ ወልድያ እና ባቲ ሆስፒታሎች እንደሚከፋፈሉም ታውቋል፡፡ ሦስቱ ሆስፒታሎች ለድንበር አካባቢዎች ቅርብ በመሆናቸው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎች የሚገቡባቸው እና ስርጭቱ ከሚታይባቸው አካባቢዎች መካከል በመሆናቸው እንደተመረጡም ተጠቅሷል፡፡
አልማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሕክምና መሣሪያ እና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም የሳኒታይዘር ማምረቻ ድርጅት አቋቁሞ ወደ ምርት መግባቱንም አቶ ዓለማየሁ አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
