
ከሚሴ: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደዋ ጨፋ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል።
በመርሐግብሩ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፣ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ.ር)፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ.ር) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)ን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በወረዳው ጎበያ ቀበሌ ስንዴን በኩታገጠም እየዘሩ አሚኮ ያገኛቸው አርሶ አደሮች ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ጊዜ እያመረቱ ተገቢውን ምርት አለማግኘታቸውን አንስተዋል። በዚህም እንደዋዛ ያሳለፉት ጊዜ እንደሚቆጫቸው ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የጤፍ ሰብላቸውን ሠብሥበው የበጋ መስኖ ስንዴን እየዘሩ ይገኛሉ። ከወራት በኋላ ስንዴውን በመሠብሠብ ሌላ ሰብል ዘርተው በዓመት ሦሥት ጊዜ የማምረት ዕቅድ ይዘዋል። ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ነው የገለጹት።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አህመድ አሊ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በበጋ መስኖ ስንዴ ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።
የማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦት መሻሻሉን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው የግብርና ሜካናይዜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ በዚህ ዓመት ከ350 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ በመሽፈን ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። እስካሁን ከ50 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በዘር ተሽፍኗል ነው ያሉት።
የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ኢትዮጵያ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች እንደኾነ ገልጸዋል። በዚህ ዓመት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
በልማቱም ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት በዘር ተሽፍኗል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳይበገሩት በግብርናው ዘርፍ እያሳየ ያለው ውጤት አበረታችም ነው ብለዋል። ግብርና ሚኒስቴርም አስፈላጊውን ድጋፍ እና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ደጀን አምባቸው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
