“ለታላቅ ሀገር፣ ታላቅ የባሕር በር”

24

ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር በር እስትንፋስ ነው ሀገራት ሕልውናቸውን የሚያኖሩበት፤ የእድገት መንገድ ነው በሥልጣኔ የሚጓዙበት፤ የጠበቀ ምሽግ ነው ሉዓላዊነታቸውን የሚያስጠብቁበት፤ ኢምባሲ ነው ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚገናኙበት፤ ፍላጎታቸውን የሚነግሩበት፤ ምኞታቸውን የሚያሳኩበት፤ የሌሎች ሀገራትን ፍላጎት እና ምኞት የሚያውቁበት።

የባሕር በር ቅንጦት አይደለም ሕይዎት ነው እንጂ። ኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የባሕር በርን የሉዓላዊነቷ፣ የደኅንነቷ እና የእድገቷ መሠረት አድርጋ ኖራለች። የባሕር ክልሏን እና የባሕር በሯን እያስጠበቀች በዓለም ላይ ገናና ታሪክ እና ሥልጣኔ አሳይታለች።

በባሕር በር የዓለምን ፖለቲካ በክንዷ ለክታለች፤ ለእርሷ ጥቅም እና ክብር በሚመጥን መልኩ እንዲኾን ተጽዕኖ ፈጥራበታለች። በዓለም የንግድ ሥርዓት የደመቀ አሻራዋን አስፍራለች። ለአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ለሚኖረው የጥቁር ዘር አርዓያ እና ምሳሌ የሚኾን ታሪክ ጽፋበታለች። ከዓለም ላይ የጸና ነጻነትን አትማበታለች።

ታዲያ ኢትዮጵያ ታላቅ እንዳትኾን የሚጥሩ ጠላቶች ኢትዮጵያን ከባሕር ክልል እና ከባሕር በር ለማራቅ ሢሠሩ ኖረዋል።

ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብ እና የመንግሥት ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ የሦሥቱ ጥንታዊ የአፍሪካ፣ የእስያ እና የአውሮፓ አሕጉራት እና ሕዝቦች የመገናኛ ጎዳና እና ድልድይ በኾነው በቀይ ባሕር እስትራቴጂያዊ ክልል የምትገኝ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር በንግድ፣ በሃይማኖት፣ በዲፕሎማሲ እና በጦርነት ጉዳዮች የቀረበ ጂኦፖለቲካዊ መስተጋብር ያላት የአፍሪካ ኃያል መንግሥት እና ሥልጣኔ ባለቤት ናት ይላሉ።

ታዲያ ከዓለም እይታ ውጭ በማይኾኑ እና እጅግ አስፈላጊ የውኃ ሀብቶች መካከል ያለችው ኢትዮጵያ የጠላት ዓይን ማረፊያ እንደኾነች ጽፈዋል።

ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ ሸለቆ ታሪካዊ ጠረፎች በኢትዮጵያ ምድር እና ሕዝብ ላይ አስከ ዛሬ ድረስ በሥፍራ እና በጊዜ ያልተቋረጠ አዲስ ጥቃት እና ጥፋት አለ ነው የሚሉት። ይህን ለመቆጣጠር ደግሞ ኢትዮጵያ ግዴታ የባሕር በር ማግኘት አለባት።

የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር መጠቀም የማይፈልጉ ጠላቶች የውስጥ ተጻራሪ ኃይሎችን በፖለቲካ፣ በገንዘብ እና በመሣሪያ በመደገፍ የሀገሪቱን ጥንታዊት እና ሉዓላዊነት ለማጥፋት ሴራ ያሴራሉ ነው የሚሉት።

ፕሮፌሰሩ ሲጽፉ ጂኦፖለቲካ በአንድ ሀገር ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ አካባቢው እና እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ መሠረታዊ የዕድገት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ወይም አፍራሽ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የጅኦግራፊ፣ የእስትራቴጂ፣ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ሁኔታዎች መግለጫ እና መስተጋብር ነው።

በዚህ ረገድ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ረጅም የነጻነት ታሪክ እንደ ዘመኑ ተጨባጭ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እና ሂደት በሀገሪቱ ብሔራዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ላይ መሠረታዊ የልማት አስተዋጽኦ እና የአፍራሽ ተጽዕኖ ፈረቃ ሲያስከትሉ ኖረዋል ነው የሚሉት።

ለወደፊቱም የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በፍጥነት አዲስ ብሔራዊ የጠረፍ ዕድገት፣ የልማት ፖሊሲ እና ፕሮግራም ቀይሶ ተግባራዊ ካላደረጉ ምናልባትም በሀገሪቱ አጠቃላይ ብሔራዊ ዕድገት እና ልማት ጉዳይ ላይ የቀይ ባሕር እና የዓባይ ሸለቆ ጂኦፖለቲካ አፍራሽ ተጽዕኖ በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችል ይኾናል ነው ያሉት።

ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ.ር) አሰብ የማን ናት በተሰኘው መጽሐፋቸው የግብፅ የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛው ፖሊሲ ኢትዮጵያ በአካባቢው የበላይነት አንዳይኖራት ከባሕሩ ዙርያ ማግለል ነው፡፡ ይህም ዓላማዋን ለማሳካት ደግሞ ኢትዮጵያን ከሚጠሉ ሀገራት እና ቡድኖች ጋር ትሠራለች። በሠራቻቸው የእጅ አዙር ሥራዎች ባለፉት ዓመታት ተሳክቶላት ቆይቷል ይላሉ። ለምን ካሉ ኢትዮጵያን ከባሕር በር አርቃት ቆይታለችና።

ግብጽ ነጻ አውጭ እና ተገንጣይ ቡድኖችን በመርዳት ኢትዮጵያ በሃብቶቿ እንዳትጠቀም ለማድረግ ስትጥር ኖራለች። አሁንም አርፋ አልተቀመጠችም። ወደፊትም አትመጥም። ምክንያቱም የእርሷን ትርፍ የምታስበው በኢትዮጵያ ኪሠራ ላይ ነውና።

ግብጽ የአረብ ሊግን በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማዳከም የማትሠራው ሥራ የላትም። ግብፅ ይህንን የምታደርገው ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ላይ ያላት መብት እና የባሕር በር መብትዋን ልታስከብር ትችላለች ከሚለው ፍራቻ በመነሳት ነው።

ግብፅ ኢትዮጵያ ፈጽሞ የባሕር በር መልሳ እንድታገኝ አትፈልግም። ለዚህ ደግሞ በስውር እና በግልጽ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ትሠራለች ነው የሚሉት። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከባሕር በር ዝግ ኾና መኖር አትችልም። የሌሎችን በጎ ፈቃድ ጠብቃ መኖርም አዳጋች ነው። ስለዚህ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማስጠበቅ ግድ ነው።

ኢትዮጵያ በሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ ባላት የመሬት ስፋት በጠቅላላው ተፈጥሮ በለገሳት እምቅ ሃብት እና በሕዝብዋ ታታሪነት የራስዋ የባሕር በር ካላት ታላቅ ሀገር መኾኗ አጠራጣሪ አይኾንም።

ወደብ አልባ ኾና ግን ድህነትን እንኳን ማሽነፏ አትችልም። በውስጥ አቅሟ ድህነትን ብትቀንስም እንኳን በዘለቄታ እይታ ታላቅ ሀገር ልትሆን አትችልም፡፡ ወደብ አልባ ኾኖ ታላቅ የኾነ ሀገር የለምና። ስለዚህ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ለመኾን የግዴታ ወደብ ያስፈልጋታል።

ኢትዮጵያ በራስዋ ወደብ አድርጋ ወደ ባሕር የመዝለቅ መብት በሰላም መፍትሔ ካልተሰጠው ወደ ፊት ለጦርነት መንስኤ እንደሚኾን አያጠራጥርም። ይህንን አደገኛ ሁኔታ ለማስቀረት ለጋስ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ድርድር መደረግ አለበት ነው የሚሉት።

የድርድሩም ውጤት መኾን የሚገባውን አሰብን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነው። ይህም ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የጦርነት መዓት ያስቀራል ይላሉ። የአሰብ ጉዳይ የተዳፈነ እሳት ማለት ነው፡፡

አማራጭ እያለህ ዝም ብለህ የምታካሄደው ጦርነት የምርጫ ጦርነት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ልትሸሸው የማትችል፣ አማራጭ የሌለው እና አስገዳጅ ጦርነት ሊገጥማት ይችላል ነው ያሉት።

ይህም የሚኾነው ታፍኖ መኖር ስለማይቻል ነው ብለው ጽፈዋል። ምርጫ የሌላት ሀገር አስገዳጅ ጦርነት ለማካሄድ ትገደዳለች፡፡ ይህ ደግሞ ጦረኝነትን ፍለጋ ሳይኾን ታፍኖ መኖር ስለማይቻል ነው። ይህ እንዳይኾን ግን ችግሮችን በውይይት እና በሰጥቶ መቀበል መርሕ መፍታት ይገባል ይላሉ።

በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር በለጠ ጓንጉል የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የዋዛ አይደለም፤ የባሕር በር ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ጥያቄ የትውልድ እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው፤ መንግሥት ይመጣል ይሄዳል፤ ሕዝብ እና ሀገር ግን ቀጣይ ናቸው፤ ሀገር ቋሚ ናት፤ የባሕር በር ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ነው ይሉታል። የባሕር በር ጉዳይ የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም፤ ይህ የሕዝብ አጀንዳ ብሔራዊ ጥቅም ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለኢትዮጵያ መቼም አይተኙላትም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ ጥረታቸውን መቀጠላቸው የማይቀር ነው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከጎረቤት ሀገራት እስከ ኃያላን የዓለም ሀገራት ይፈተናል፤ ይህ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ በአንድነት መነሳት ያስፈልጋል ነው የሚሉት።

የባሕር በር ጉዳይ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሲብላላ የነበረ፣ አንገብጋቢ ነው፤ ይህ የመኖር እና ያለ መኖር ጉዳይ ስለኾነ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት አለብን ይላሉ።

የምሥራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ስበት ኃይል የምትቆጣጠረው ኢትዮጵያ የባሕር በር ካገኘች የበላይነቷን የበለጠ ታጠናክራለች። የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ኢ ተገማች ነው የሚሉት መምህሩ ነገሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ የበቃ እና የነቃ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለታላቅ ሀገር፣ ታላቅ የባሕር በር ያስፈልጋል እና በአንድነት፣ በመግባባት በመቆም የኢትዮጵያን ጥያቄ ማስመለስ ግድ ይላል። ስለ ምን ካሉ ኢትዮጵያ ተዘግታ መኖር አትችልምና።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ሕዝቦቻችን የሚጠቅም የትብብር ድልድይ እየገነባን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ
Next articleበኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት እየተሠራ ነው።