“በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ሕዝቦቻችን የሚጠቅም የትብብር ድልድይ እየገነባን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ

9

ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ ኢትዮጵያን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ.ር) አመሰገኑ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ባደረግሁት ይፋዊ ጉብኝት ላደረጉልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል አመሰግናለሁ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ትብብርን በማጠናከር እና ለንግድ ሥራዎቻችን አዳዲስ በሮችን በመክፈት ረገድ ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል የጋራ ቁልፍ ዘርፎቻችን በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት አድርገናልም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሲንጋፖር በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት የወሰደችውን ውሳኔ በደስታ ተቀብለዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዎንግ ይህም ትልቅ የትብብር ምዕራፍን ይከፍታል ነው ያሉት፡፡

የኤምባሲው በአዲስ አበባ መከፈት ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይኾን ከአፍሪካ ኅብረት እና ከሰፊው የአፍሪካ አሕጉር ጋር ወሳኝ ትስስር ኾኖ ያገለግላልም ብለዋል።

ሲንጋፖር እና ኢትዮጵያ ሁለቱም ወደየ አሕጉሮቻችን መዳረሻ የሚወስዱ በሮች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትብብሮቻችንን በማጠናከር “ለቀጣዮቹ ዓመታት ሕዝቦቻችንን የሚጠቅም በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ድልድይ እየገነባን ነው” ብለዋል።

በታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡት ዘግይተውም ቢኾን እውነታውን የተረዱት ናቸው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)
Next article“ለታላቅ ሀገር፣ ታላቅ የባሕር በር”