“የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡት ዘግይተውም ቢኾን እውነታውን የተረዱት ናቸው” እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)

7

ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት የከፋ ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሳንካዎችን ፈጥሯል፡፡ ከወትሮው በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ግጭት የጦርነት ዳፋ ዋጋ የከፈለው ክልሉ ሌላ የጦርነት እና የግጭት ነጋሪት ተጎስሞበት ጉዳቱን ሥር የሰደደ አድርጎበታል፡፡

በክልሉ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ማግስት ጀምሮ የመንግሥታዊ ተቋማት አገልግሎቶች ተቋርጠው፣ በርካታ የክልሉ አካባቢዎች በታጠቁ ኃይሎች ስር ወድቀው እና የሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት አደጋ ውስጥ ወድቆ ቆይቶ ነበር፡፡

የክልሉ መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ሕግ በማስከበራቸው እና የክልሉ መንግሥት ባቀረበው የሰላም ጥሪ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን በመቀበላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ በበርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ምክንያት ኾኗል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት እና የሰላም እጦት ክልሉን ከማዳከም የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የተረዱ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችም ግጭቱ ቆሞ የሰላም አማራጮች እንዲፈለጉ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጠይቀዋል፡፡ “ያለፈው አልፏል” ከደረሰው ጉዳት ተምረን ቀጣዩን በጋራ ማስተካከል እና ማረም ይኖርብናል ያለው የክልሉ መንግሥትም ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪዎችን እና አማራጮችን አቅርቧል፡፡

ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ ወቅታዊ ሰላም ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) በክልሉ ያለው ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡ የታየው ሰላም የጸጥታ ተቋማትን በማጠናከር፣ በተደጋጋሚ ሕዝቡን በማወያየት እና የሰላም አማራጮችን በማስፋት የተገኘ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ ከግጭቱ ማግስት ጀምሮ በጸጥታ ተቋማት ላይ የተደረጉ ሪፎርሞች የመፈጸም አቅምን ያሻሻሉ ነበሩም ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ተከትሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጮችን እየተቀበሉ ገብተዋል ያሉት ኀላፊው “የሰላም ጥሪውን ተቀብለው የገቡት ዘግይተውም ቢኾን እውነታውን የተረዱት ናቸው” ነው ያሉት፡፡ በአማራ ሕዝብ ስም ነፍጥ ያነሳው ቡድን መዳረሻው የሕዝብ ነጻነት ሳይኾን የግል ጥቅም እና ዝርፊያ እንደነበር ብዙዎቹ ዘግይተውም ቢኾን መረዳታቸውን አንስተዋል፡፡

ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ታጣቂዎች የሰላም አማራጮችን እየተቀበሉ መግባታቸውን ጠቁመዋል። የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው የክልሉ መንግሥት እና ሕዝብ የሰላም አቅም መኾን መቻላቸውንም አንስተዋል፡፡

ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ገብተው እና ሠልጥነው በመረጡት መስክ እንዲሰማሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የሰላም አማራጮችን ተቀብለው የሚገቡ ታጣቂዎች የክልሉ የልማት አቅም እንዲኾኑ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሰላም አማራጮችን የተቀበሉ ታጣቂዎችን በዘላቂ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም አንስተዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጮችን ተቀብለው ሥልጠና መውሰዳቸውን ያነሱት ኀላፊው አሁንም በየጊዜው የሰላም አማራጮችን እየተቀበሉ የገቡ ታጣቂዎች ሥልጠና ይወስዳሉ ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ሂደቱን የሚከታተል እና የሚደግፍ ተቋም አቋቁሞ እና ኀላፊነት ሰጥቶ እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ያለው የክልሉ ሰላም ተሰፋ ሰጪ እንደኾነ ያነሱት ኀላፊው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ታጣቂዎችም የሰላም አማራጮችን ተቀብለው ሀገራቸውን በማልማት ራሳቸውን መቀየር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትጥቅ ትግል ሰላምን አያረጋግጥም።
Next article“በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ሕዝቦቻችን የሚጠቅም የትብብር ድልድይ እየገነባን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ