
ፍኖተ ሰላም: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችን በማገናኘት የሁለቱን ክልሎች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መሥተጋብርን እንደሚያጠናክር ተስፋ የተጣለበት የነቀምት – አጋምሳ – ቡሬ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ወደ ሥራ የገባው በ2012 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር።
በ2015 ዓ.ም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ቾንኪነግ ኢንርናሽናል ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሸን የተባለ የቻይና ተቋራጭ ውሉን ፈፅሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይሁንም እንጂ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሂደት ላይ ሳለ በተለያዩ ወቅታዊ ችግሮች በመቋረጡ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንዳልተቻለ የፕሮጀክቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኑርልኝ ቢተው ለአሚኮ ተናግረዋል።
ተቋርጦ የቆየው ፕሮጀክቱ በታኅሣሥ 2017 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ ወደ ግንባታ በመግባት አሁን ላይ የአስፋልት ማንጠፍ፣ የመሬት ቆረጣ፣ የአካፋይ መንገድ ግንባታ እና ሌሎች ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መኾናቸውን አመላክተዋል።
በፕሮጀክቱ አጠቃላይ ከሚገነባው 84 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ሥራ 54 ኪሎሜትር የሚኾነው ግንባታ መከናወኑን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ጠቁመዋል። የፕሮጀክት አፈፃፀም 63 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል።
ፕሮጀክቱን በቀጣይ አንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የነቀምት – አጋምሳ – ቡሬ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በፌደራል መንግሥት በጀት እና በወርልድ ባንክ ድጋፍ በ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ መኾኑ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
