
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አንደኛ ዓመት የሰማዕትነት ቀን ዛሬ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ እየታሰበ ነው፡፡ በዞኑ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዕለቱ የታሰበው በጧፍ ማብራት እና በፓናል ውይይት ነው።
መሥዋዕትነትን የተቀበሉ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለአማራ ክልል ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ሰላም እና ሁለንተናዊ ዕድገት የተሰለፉ ግንባር ቀደም መሪዎች እንደነበሩ በውይይቱ ተነስቷል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጋሻው አንዳርጌ (ፕሮፌሰር) “የሕዝብና የሀገር ፍቅር፣ ኃላፊነት እስከ መሥዋዕትነት” በሚል ርእስ የቀድሞ የክልሉ መሪዎችን የተመለከተ የመወያያ መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል። ፕሮፌሰር ጋሻው “ምንም እንኳን በሞታቸው ሐዘን እና ቁጭት ቢሰማንም ለቆሙለት ዓላማ መሥዋዕትነትን በመክፈላቸው እንኮራባቸዋለን” ብለዋል። መሪዎቹ ለሕዝባቸውና ለዓላማቸው መሥዋዕት ሆነው ማለፋቸውንም አስታውሰዋል። መሥዋዕትነት የከፈሉለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ እንደሚገባም መክረዋል።
የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ ሥርዓት፣ ግፍ እና የሰው ልጆች ጭቆናን ለነፍሳቸው ሳይሰስቱ በጽናት መታገላቸው ለትውልዱ ትምህርት እንደሚሆንም ተናግረዋል። ለሕዝብ እና ለሀገር ክብር እስከ መሥዋዕትነት መታገል ካለፉ መሪዎች መማር እንደሚገባ እና ከዚህ በመነሳት ትውልዱ በተሠማራባቸው የሥራ ዘርፎች ውጤታማ ሥራ መሥራት፣ ሕዝብ እና ሀገርን ማልማት እንደሚገባውም መክረዋል። መሥዋዕትነት የከፈሉት መሪዎች አሁን ላለው ትውልድ በብዙ መልኩ ተምሳሌት እንደሆኑ በመግለጽም ቀጣዩ ትውልድ የሞቱለትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።
አብመድ ያነጋገራቸው የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ትውልዱ ከመሪዎቹ ለዓላማ ጽናት እና ላመኑበት ነገር መሥዋዕትነትን መክፈልን ሊማር ይገባል ብለዋል፡፡ ያልተመለሱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በጽናት መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ደግሞ መሪዎቹ ፍትሐዊ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት እና ወደኋላ የቀሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ የታገሉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የሠለጠነ አመራር በመስጠት ወጣቶች ሰላማቸውን እንዲያስጠብቁ እና አጀንዳቸው ልማት ላይ ብቻ እንዲሆን በማድረግ የመሪዎቹን ራዕይ ለማሳካት እየተሠራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የቀድሞው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶክተር) ወንድም አቶ ሽሽግ መኮንን ደግሞ ‘‘ፍትህ ሊሟላ ይገባዋል’’ ብለዋል፡፡ አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነትን ትውልዱ ሊወርስ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ሽሽግ ‘‘ሕይወታቸውን ያጡ መሪዎች ፍትሕ ማግኘት አለባቸው’’ ሲሉም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ-ከደብረታቦር
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
