የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብርን ለማስፍት እየተሠራ ነው።

14
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በድመት ገደል ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ተጀምሯል።
በዚህም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳያቋርጡ እና የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸው የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገልጿል።
የተማሪ ወላጆች በበኩላቸው የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በመጀመሩ መደሰታቸውን ጠቁመው ቀጣይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የሁለት እጁ እነሴ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ተስፋ አዲስ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የተጀመረው በድመት ገደል ትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኙ ቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ሲኾን በቀጣይ ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማትም የሚቀጥል ይኾናል ብለዋል።
በቀጣይ ትምህርት ቤቶች በባለቤትነት ይዘው በውጤታማነት እንዲያስቀጥሉት ከተማሪ ወላጆች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይና የአሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የፀዳው አስማረ በበኩላቸው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መጀመሩ ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አቀባበል እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል።
ፕሮግራሙን በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ለማስቀጠል በጀት ተመድቦ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ከቅድመ መደበኛ ተማሪዎች በተጨማሪ ሌሎች ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ፕሮግራሙን አጠናክሮ ለመቀጠል የተቋቋመውን ኮሚቴ በማገዝ እና ሃብት በማፈላለግ በኩል የአካባቢው ማኅበረሰብ፣ የትምህርት ባለድርሻዎች እና ሌሎችም የጋራ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን ግንኙነት የሚያሳይ ነው።
Next articleበኩር ጋዜጣ ኀዳር 15/2018 ዓ.ም