በሥርዓተ ምግብ ትግበራ የተሻሉ መንደሮችን የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

11

እንጅባራ: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የተቀናጀ ግብርናን በመተግበር የአመጋገብ ሥርዓታቸውን ማሻሻላቸውን በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዚገም ወረዳ የጉንጋና ዲኺ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

 

በወረዳው በሥርዓተ ምግብ፣ በቤት አያያዝ እና በሥርዓተ ጾታ ትግበራ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ የአርሶ አደሮች ሞዴል መንደር ተመርቋል።

 

ዚገም ወረዳ የጉንጋ እና ዲኺ ቀበሌ አልጋም ጎጥ ነዋሪዎቹ አርሶ አደር ክንዴ ኃይሉ እና አርሶ አደር ዓለማየሁ ጌታሁን አካባቢያቸው የሰጡትን ሁሉ አብቃይ፣ ትርፍ አምራች ቢኾንም ትኩረታቸው ውስን ዓመታዊ ሰብሎችን ብቻ ማምረት እንደነበር አንስተዋል። ያመረቱትንም ቢኾን የሚመገቡት ከገበያ የተረፈውን ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።

 

ይህም በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት

በተደጋጋሚ ለተለያዩ የጤና እክሎች ሲዳርጋቸው መቆየቱን ነው ያነሱት።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በባለሙያዎች በተደረገላቸው ተከታታይ የሙያ ድጋፍ የተቀናጀ ግብርናን በአካባቢያቸው በመተግበር ዓሣን ጨምሮ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን የማዕዳቸው አካል ማድረግ መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

 

መንደራቸው ባስመዝገበው ውጤት ለሌሎች አርሶ አደሮች የተሞክሮ ማዕከል መኾኑን ተናግረዋል።

 

የዚገም ወረዳ ግብርና ጽሕፍት ቤት ኀላፊ ዳንኤል ሞላ (ዶ.ር) ወረዳው ትርፍ አምራች እና ሁሉን አብቃይ ቢኾንም በኅብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ ምክንያት በርካታ ሕጻናት የመቀንጨር ሰለባ መኾናቸውን ተናግረዋል።

 

የኅብረተሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ለማሻሻል በሥርዓተ ምግብ ትግበራ ሞዴል የኾኑ መንደሮችን የመፍጠር ሥራ እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል። እየተወሰዱ ባሉ እርምጃዎችም ተስፋ ሰጭ ለውጦች እየታዩ መኾናቸውንም ገልጸዋል።

 

ለምረቃ በበቃው አልጋም ጎጥ የሚገኙ 79 አርሶ አደሮች መንደርም በሥርዓተ ምግብ፣ በሥርዓተ ጾታ እና በቤት አያያዝ የተሻለ ሞዴል እንደኾነም አብራርተዋል።

 

ይህንን መልካም ተሞክሮ ወደ ሌሎችም ቀበሌዎች በማስፋት በአካል እና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ ለመገንባት በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት።

 

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ነጋ መከተ ሞዴል መንደሩ ለሌሎች አካባቢዎችም በአርዓያነት የሚጠቀስ መኾኑን ተናግረዋል።

 

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በሁሉም ወረዳዎች በሥርዓተ ምግብ እና በሥርዓተ ጾታ ትግበራ የተሻሉ መንደሮችን የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

 

ዘጋቢ:- ሳሙኤል አማረ

 

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

👇👇👇

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

 

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል ከሁሉም ይጠበቃል።
Next article“ከሲንጋፖር ጋር ይኽን የወዳጅነት እና የትብብር ጉዞ በጋራ በመቀጠላችን ክብር ይሰማናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)