ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል ከሁሉም ይጠበቃል።

31
አዲስ አበባ: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት ጋር በመኾን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ንቅናቄን አስጀምሯል።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሙና አሕመድ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሀገራችን ሴቶች በየዘርፉ በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ውስጥ በንቃት የመሳተፍ ድርሻቸውን እንደሚያሳንሰው ገልጸዋል።
ከሚገኘው የልማት ትሩፋት እኩል ተቋዳሽ እንዳይኾኑ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑት ሕጻናትን መጻኢ ተስፋን እንደሚያጨልምም አንስተዋል።
የልማት ቅብብሎሹ ከትውልድ ወደ ትውልድ በተሳካ መልኩ እንዳይካሄድ የሚያደርግ ተግባር በመኾኑ ሁላችንም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን አጥብቀን ልናወግዘው ይገባል ብለዋል፡፡
ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች እና ሕጻናት ላይ አካላዊ ጉዳት የሚያደርሱ፣ የከፋ የጤና እክል የሚያስከትሉ፣ ውስብስብ እና ድርብርብ ለኾኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚዳርጉ ናቸው ነው ያሉት።
ይህ ብቻም ሳይኾን ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላም በተጎጂዎች አዕምሮ እና ሥነ ልቦና ላይ ጥሎት የሚያልፈው ጠበሳ በቀላሉ የሚሽር አይደለም ብለዋል። ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በአመለካከትም ኾነ ድርጊቱን ለመከላከል እና ሙሉ በሙሉ ለማስቆም በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
መንግሥት ለሴቶች እና ሕጻናት ሰብዓዊ መብት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ተቀብሎ ከማጽደቅ ባሻገር አላሠራ ያሉ ሕጎችን ለማሻሻል፣ አዳዲስ የአሠራር እና የአደረጃጀት ለውጦችን ለማካሄድ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
የተቋማትን አቅም ለማጠናከር፣ የተቀረጹ የሕግ ማዕቀፎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ፣ ስኬታማ እንዲኾኑ ጠንካራ ሕጋዊ እና አሥተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል ነው ያሉት።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል፣ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እና ምላሽ ለመስጠት ሀገር አቀፍ የአሠራር ሥርዓቶችን እየተገበረ እንደኾነም አንስተዋል።
ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት የጉዳይ አሥተዳደር እና የአገልግለት አሰጣጥ መመሪያ፣ የቅብብሎሽ አገልግሎትን ጨምሮ የተቀናጀ እና ሁለገብ የምርመራና የሕክምና፣ የሕግ ድጋፍ እና የሥነ ልቦና ድጋፍ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት የአንድ ማዕከል ጊዜያዊ ማረፊያ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
ተጎጂዎች ከጉዳታቸው እስኪያገግሙ የሚቆዩበት ማዕከላት እንዲቋቋሙ እና እንዲስፋፉ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ሠፋፊ ሥራዎችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስነ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) ጋር በመኾን ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት አያያዝ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል የሰርቨር፣ የአይሲቲ፣ የባለሙዎች ሥልጠና እና ሌሎች
አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በማጠናቀቅ ላይ እንደኾነም ተናግረዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም ከጥቃት ጋር በተያያዘ ይገጥም የነበረውን የመረጃ ክፍተት እንደሚቀርፍ አንስተዋል።
ከዓለም ባንክ በተገኘ ፕሮጀክት በተመረጡ ክልሎች፣ ጤና እና ፍትሕ ሚኒስቴር ተጨማሪ በጀት እንዲያገኙ በዕቅድ ውሰጥ በማካተት ጠንካራ የመከላከል እና ጥራት ያለው የምላሽ አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ሴቶችን እና ሕጻናትን ከጥቃት ለመከላከል እና ለማስቆም በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልኾኑ አጋር አካላት የጋራ ጥረት በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። ነገር ግን አሁንም ድርጊቱ እየተፈጸመ መኾኑን አንስተዋል። የተጀመረው ርብርብ ከምንጊዜውም በበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የንቅናቄ መርሐ ግብሩ “ጥቃትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ለሚቀጥሉት 16 ቀናት ይቆያል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ
Next articleበሥርዓተ ምግብ ትግበራ የተሻሉ መንደሮችን የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።