የወባ በሽታ ለምን ለዘመናት ስጋት ኾኖ ቀጠለ ?

7
ባሕር ዳር: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ወባ በጥገኛ ተህዋስያን ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ ለዘመናት የሕዝብ የጤና ስጋት ኾኖ ዘልቋል። ለዓመታት ወባን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ተሠርቷል። ነገር ግን ዛሬም ድረስ ወባ በኢትዮጵያ
የሕዝብ ስጋት ኾኖ ቀጥሏል።
በዚያኔው አጠራር በሰሜን በጌ ምድር ክፍለ ሀገር በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጤና ጣቢያ እንደኾነ ይነገራል።
ለጤና ጣቢያው መመሥረት ዐቢይ ምክንያቱ በወቅቱ በደንቢያ እና በበለሳ ወረዳዎች የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ነበር ይባላል። በዚያ የዘመን የነበረው የወባ ወረርሽ ሕዝብን ክፉኛ የጎዳ ነበር። በእርግጥ የወባ በሽታ በዚያ አካባቢ ከእነ አጼ ሱስንዮስ ዘመን ጀምሮ ስጋት እንደኾነ ይነገራል። አጼ ሱስንዮስ በጎርጎራ ጣና ዳርቻ ያሠሩትን ቤተ መንግሥት ለቅቀው ወደ ደንቀዝ ያቀኑት በዚያኔው አጠራር ንዳድ (ወባ) አስቸግሯቸው ነው ይባላል። እንግዲህ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ወይም ከዚህ ቀድሞ ከነበሩ ዘመናት ጀምሮ ወባ በዚያ ሥፍራ ስጋት ኾኖ ቀጥሏል ማለት ነው።
ካሳሁን አያናው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ቆላ ድባ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የሕመም ስሜት ተሰምቷቸው ቆላ ድባ ጤና ጣቢያ ለሕክምና መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ምርመራ በማድረግም የወባ በሽታ እንደተገኘባቸው እና መድኃኒት እንደታዘዘላቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በመሥራት እና አጎበርን በመጠቀም ወባን መከላከል እንደሚቻል ከጤና ባለሙያዎች ምክረ ሀሳብ ተቀብያለሁ፤ የተሰጠኝን ምክረ ሀሳብ ተግባራዊ በማድረግ ወባን ለመከላከል ጥረት አደርጋለሁ ነው ያሉት፡፡
ሌላኛዋ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ፈንታነሽ ያያ ናቸው ፡፡ እሳቸውም የሕመም ስሜት ተሰምቷቸው ለሕክምና ወደ ጤና ጣቢያው እንደሄዱ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸውም ኾነ ቤተሰቦቻቸው በወባ በሽታ በተደጋጋሚ እንደሚጠቁ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ከእርሳቸው ውጭ አራት ቤተሰቦቻቸው በወባ በሽታ መያዛቸውን አንስተዋል።
የምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጦይባ አሕመድ በአካባቢው የወባ በሽታ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ መሠራጨት ዋነኛ ምክንያት የአካባቢው የአየር ንብረት ለወባ መራባት ምቹ መኾን ነው ይላሉ። የአካባቢው የቦታ አቀማመጥ ረግረጋማ መኾንም ለወባ በሽታ መራባት ምክንያት ነው ብለዋል።
ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ግን በፊት ከነበረበት የበሽተኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እየቀነሰ መምጣቱን አንስተዋል።
ወረርሽኙ ሊቀንስ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት በወረዳው ካሉ 34 ቀበሌዎች ውስጥ ሥርጭቱ የሚበዛባቸውን በመለየት በ23 ቀበሌዎች የኬሚካል ርጭት በመካሄዱ፣
በቀሪዎቹ ቀበሌዎች የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በመሠራቱ ነው ብለዋል።
ማኅበረሰቡ አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ በመፈጠሩ፣ በአካባቢያቸው የሚገኙ ያቆሩ ውኃዎችን በማፋሰስ እና የማይፋሰሱት ላይ ደግሞ ኬሚካሎችን በመጨመር ትኩረት ተሰጥቶባቸው በተሠሩ ሥራዎች እንደኾነም አብራርተዋል፡፡
በጎንደር ዩንቨርሲቲ የሕክም እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ የጤና ሥርአት እና ፖሊሲ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አምሳሉ ፈለቀ የወባ በሽታን ለመከላከል በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የጤና ጣብያ ተቋቁሞ ሲሠራ መኖሩን አንስተዋል።
በዚያ ዘመን በአካባቢው የተከሰተው ወረርሽኝ የከፋ መኾኑን ለማሳየት “የት ትሄዳለህ? በለሳ ሰኔል አለያዝክም እሳ” የሚባል አባባል እንደነበር ነው የተናገሩት። ይህ የሚያሳየው ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚሄዱ ሰዎች በወባ ስለሚጠቁ እና ሕክምናውም እምብዛም በመኾኑ ደርሶ መመለስ እንደማይቻል ለማሳየት ነበር ይላሉ።
በወቅቱ እስከ 7ሺህ ሰዎች በቀን ይሞቱ እንደነበረ ታሪካዊ መረጃዎች ያመላክታሉ ነው ያሉት።
ከዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው በወቅቱ የጤና ሥርዓቱ የተዳከመ እና ጭራሹንም የሌለ በመኾኑ እንደነበርም ገልጸዋል።
በግርማዊ ቀዳማዊ አጼ የተመሠረችው ጤና ጣብያ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ መመሥረት እንደ መነሻ ናት ይባላል።
በዚህ ምክንያት የተመሠረተው የጎንደር ዩንቨርሲቲ በአካባቢው ሥራ ሲሠራ ኖሯል። ለተማሪዎች የመስክ ሥራ በተለይ ለተመራቂ ተማሪዎች ልምምድ ማድረግ አስፈላጊ በመኾኑ የቆላ ድባ ጤና ጣቢያ ጋር ግንኙነቱ እና አሠራሩ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ኾነ ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
በዚህም ማንኛውም የጤና አጠባበቅ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የሚካሄደው በተማሪዎች ነበር ብለዋል። ተማሪዎቹ ከሚያከናውኗቸው የጤና አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የወረርሽ በሽታዎችን ማከም፣ መቆጣጠር እና መከላከል ነበር ነው ያሉት።
ወባ ዋናው በአካባቢው የሚከሰት እና የብዙዎችን ሕይዎት የሚቀጥፍ በሽታ በመኾኑ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራበትም ነበር ብለዋል ፕሮፌሰሩ። ተማሪዎቹ በቡድን ኾነው በሽታው ከተከሰተበት አካባቢ በመገኘት እና ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን ያከናውኑ እንደነበርም ገልጸዋል።
ኾኖም ጤና ጣቢያው ከተመሠረተ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢኾንም እስካሁን ወባ ለአካባቢው ችግር ኾኖ ዘልቋል ይላሉ።
በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የጤና አጠባበቅ ትምህርቶች ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ወስዶ ተግባራዊ አለማድረግ፣ ሰዎች የሚኖሩበትን አካባቢ መቆጣጠር አለመቻላቸው፣ ደንቢያ በአብዛኛው ረግረጋማ በመኾኑ የታቆሩ ውኃዎች በስፋት መኖር ችግሩ ለመቀጠሉ ምክንያቶች እንደኾኑም አብራርተዋል።
ባለሙያዎች የሚያዙትን መድኃኒት በትክክል አለመውሰድ፣ የአልጋ አጎበርን በትክክል አለመጠቀም፣ በኬሚካል የተረጩ ቤቶችን በአግባቡ አለመያዝ፣
አጎራባች አካባቢዎች ተመሳሳይ ቁጥጥር እና የመከላከል ስልትን ተግባራዊ አለማድረግም ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት ችግሩ የሁላችን በመኾኑ እስካሁን ዋጋ ያስከፈሉንን ችግሮች በሚገባ በመለየት እና ተቆራርጦ መፍትሔው ላይ መዝመት ያስፈልጋል።
የጤና ልማት እና የጸረ ወባ ማኅበር መሥራች እና ዋና ዳይሬክተር አበረ ምህረቴ (ዶ.ር) በደንቢያም ኾነ በሀገሪቱ ላይ የሚከሰቱ የወባ ወረርሽኞችን ለመግታት የተጠና ጥናት የለም ይላሉ። በኢትዮጵያ የወባ ወረርሽኝ ለምን አይጠፋም? ካልን ኅብረተሰቡ ስለ ጤና ያለው ግንዛቤ ደካማ መኾን ነው ብለዋል፡፡
ወባ የሚከሰትባቸው አብዛኛዎቹ ወቅቶች ገበሬው በከፍተኛ ሁኔታ ሥራ ላይ በተጠመደበት ወቅት በመኾኑ ስለ ጤንነቱ ሳይኾን ቅድሚያ ስለ ሥራው በማሰብ እና በመዘናጋት ምክንያት በከፍተኛ ቁጥር በበሽታው የመጠቃት ሁኔታ ይታያል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በመነሳት በሽታውን ለመቆጣጣር የባሕሪ ለውጥ መምጣት አለበት ነው የሚሉት። በእያንዳንዱ ማኅበረሰብ ላይ የባሕሪ ለውጥ እንዲመጣ በትኩረት ሥራ መሥራት ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡
ማንኛውም ሰው ያቆረ ውኃ ሲያይ ይህንን ማዳፈን የኔ ጉዳይ ነው ብሎ ማሰብ እስኪችል ድረስ ግንዛቤ መፍጠር ይኖርብናል፤ ይህንን ማድረግ ስንችል ነው ወባን ልንቆጣጠር ወይም መግታት የምንችለው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ ፕሮግራም አሥተባባሪ ዳምጤ ላንክር የወባ በሽታ የኅብረተሰብ ጤና ችግር ኾኖ ቆይቷል ይላሉ።
ሥርጭቱ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ ቢኖርም የ2018 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር በተወሰነ መልኩ የመቀነስ አዝማሚያ አምጥቷል ብለዋል፡፡
ተጋላጭ ከኾኑት ወረዳዎች ውስጥ በዋናነት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች ናቸው ያሉት አሥተባባሪው ከነዚህ ውስጥም ምሥራቅ ደንቢያ አንዱ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡
ምሥራቅ ደንቢያ ቀደም ባሉት ዓመታት በክልሉ ካሉ ወረዳዎች በወባ ወረርሽኝ የመጀመሪያ እና የሞት ምጣኔውም ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
ከዛ በመነሳት ወባን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ሁሉም አይነት ስልቶችን በመጠቀም ወረርሽኙ ቀንሶ እንደሌሎች ወረዳዎች ችግር የኾነበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በአማራ ክልል በ2018 በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡ ምርመራ ከተደረገላቸው ውስጥ ከ586 ሺህ በላይ የሚኾኑ ሰዎች የወባ በሽታ ተገኝቶባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ይህ ቁጥር ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየ ቢኾንም አሁንም ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
በክልሉ ካሉ እና ጫና የሚበዛባቸው ተብለው በተለዩ 26 ወረዳዎችም የአጎበር ሥርጭት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ማኅበረሰቡም የአጎበር አጠቃቀሙን እንዲያጎለብት የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በወባ መከላከል እና ተግባር ላይ ዋና ተሳታፊ በመኾን ለማኅበረሰቡ ወባን የመከላከል ስልቶች ላይ ያለውን ግንዛቤ እንዲጨምር በማድረግ የማኅበረሰብ ችግር እንዳይኾን ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleሕጻናት ላይ መሥራት ሀገርን መገንባት ነው።
Next articleየተጠባባቂ ጥሪ ማስታወቂያ