
ገንዳ ውኃ: ኅዳር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን “የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት የሕጻናት ቀን በገንዳ ውኃ ከተማ ተከብሯል።
ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
የገንዳ ውኃ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ከዞኑ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ጋር በጋራ በመኾን ነው በዓሉን አስበው የዋሉት።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ሴቶች፣ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ የመምሪያው ኀላፊ ተወካይ እና የሕጻናት ባለሙያው መንግሥቱ አለማየሁ አብዛኛውን ጊዜ ሕጻናት ለችግር ተጠቂዎች እና ተጎጅዎች ስለኾኑ ይህን ለመከላከል እና መብቶቻቸውን ለማስከበር ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ስለኾኑ ዛሬ ላይ በሚገባ በሥነ ምግባር ኮትኩቶ እና አንጾ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት። ሕጻናት ላይ መሥራት ሀገርን መገንባት እና ማነጽ መኾኑንም ገልጸዋል።
በሕጻናት ላይ ጉዳት የሚያደረሱ አካላትን ለሕግ ቀርበው ተጠያቂ እንዲኾኑ እና እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው ከፍትሕ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
በተለይ በአስገድዶ መድፈር የተሰማሩ ወንጀለኞችን በሕግ ቀርበው የፍርድ ውሳኔ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት።
የገንዳ ውኃ ከተማ ቁጥር ሁለት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአማርኛ ቋንቋ እና በትምህርት ቤቱ በተጓዳኝ ክበባት የሴቶች እና ሕጻናት ተጠሪ መምህርት ትዕግስት አየለ ሕጻናት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው በክበቡ የተለያዩ ድጋፎችን እና ግንዛቤዎችን እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
በቤተሰብ ምክንያት ያለዕድሜያቸው የሚያገቡ ሕጻናትን ተማሪዎች ጥቆማ እንዲሰጡ በማድረግ እና ችግሩን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የሕጻናትን መብት እያስከበርን ነው ብለዋል።
ሕጻናት ትኩረታቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲኾንም ሥራዎችን እያከናወኑ እንደኾነም ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ሕጻናት ቀኑ በመከበሩ ደስ እንዳላቸው ተናግረዋል። መብታችን እና ግዴታችን እንድናውቅም አስችሎናል ነው ያሉት።
የመማር፣ የመኖር፣ የመጫወት እና የተለያዩ መብቶቻቸው እና ጥቅማቸው እንዲከበሩላቸውም ተሳታፊ ሕጻናት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
