ምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ ወረራ ስጋት ተደቅኖበታል፡፡

225

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) እንደሌላው የዓለም ክፍል በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተፈተነ የሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ለሦስተኛ ጊዜ መጋለጡ ታውቋል፡፡ ሲ ጂ ቲ ኤን እንደዘገበው የበረሃ አንበጣው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሆኖ በኬንያ ሰብል ማውደም ጀምሯል፤ ይህም ሚሊዮኖችን በቀጣናው ለርሀብ እንዳይዳርግ ተሰግቷል፡፡

ምንም እንኳ በኬሚካል ለመቆጣጠር ጥረቶች ቢደረጉም ምቹ የአየር ሁኔታ ያጋጠመው የበረሃ አንበጣ በቅርብ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ቀጣናውን ሊያካልል ለመብረር እየተዘጋጀ ስለመሆኑም ነው የተነገረው፡፡

የዓለማቀፉ የአደጋ ታዳጊ ኮሚቴ በዚህ ወር ያወጣው ሪፖርት ‘‘በቀጣናው በአስር ሺዎች ሄክታር ላይ የነበረ ሰብልና የእንስሳት መኖ ወድሟል’’ ብሏል፤ አነስተኛ የሚባለው የአንበጣ መንጋ በቀን የ35 ሺህ ሰዎችን የምግብ ፍጆታ ያህል እንደሚያወድም በመግለጽ፡፡

ሲ ጂ ቲ ኤን እንዳስታወቀው በኢትዮጵያም በጥርና ሚያዝያ አካባቢ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ በ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረ የእንስሳት መኖ እና በ200 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ ሰብል አውድሟል፡፡ በዚህም 350 ሺህ ቶን ምግብ እንደወደመ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በሰኔ ሪፖርቱ ይፋ ማድረጉን ዘገባው አስታሷል፡፡ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቂ መረጃ አለመሰብሰቡን ያመለከተው ሪፖርቱ የጉዳቱ መጠን ከዚህም ሊያልፍ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡

ከኢጋድ የአየር ሁኔታ ክትትል ፕሮግራም ለሲ ጂ ቲ ኤን ሐሳብ የሰጡት ኬንት ኬሙቺ ምዋንጊ ‘‘ተጨማሪ መረጃዎች እስካልቀረቡ ድረስ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ክፉኛ በበረሃ አንበጣው የተጎዳችው ኢትዮጵያ ነች፤ በመቀጠል ደግሞ ሶማሊያ’’ ብለዋል፡፡

ሶማሊያ በየካቲት በበረሃ አንበጣ መንጋ በመወረሯ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥታ ሁሉ ነበር፤ በቅርቡ ግን በሶማሊያና ኬንያ የጣለ ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በመፈልፈል ላይ የነበረውን መንጋ አጥፍቶ ስጋቱን ቀንሶላቸዋል፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳና ቡሩንዲ የኬሚካል ርጭት አድርገው የበረሃ አንበጣ መንጋውን መቆጣጠር ችለዋል፡፡

የዓለም ባንክ ባለፈው ወር ለበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ተጋላጭ ለሆኑ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አድርጎ ነበር፡፡

ከየካቲት ጀምሮ የኬሚካል ርጭት ሥራዎች መቀጠላቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ይህም ከነበረበት እስከ 20 እጥፍ መጠኑ ይጨምር ነበረውን መቀነሱን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡ ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት አራት ወራት ብቻ ከ400 ሺህ ሄክታር ያላነሰ መሬት ላይ የኬሚካል ርጭት ተደር እስከ 400 ሚሊዮን የሚቆጠር የበረሃ አንበጣ መገደሉን በኬንያ ናይሮቢ የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት ተወካይ አስታውቀዋል፡፡ ‘‘በእርግጥ የተወሰኑ የሶማሊያ አካባቢዎችን መድረስ ስለማንችል በትክክል ለማወቅ እንቸገራለን፤ በእርግጠኝነት ግን ከፍተኛውን ስጋት ለመቀነስ ችለናል’’ ብለዋል ተወካዩ፡፡

በኬንያ ሰሜናዊ የጠረፍ አካባቢዎች ባሉ ደረቃማ ቦታዎች የበረሃ አንበጣ መንጋ መታዬቱ ታውቋል፡፡ ይህም በመብረር ወደሌሎ አካባቢዎች እንዳይሠራጭ ተሰግቷል፡፡
ትንበያዎች እንደሚያመለክቱት በተለይ ከሰኔ አጋማሽ አንስቶ እስከ ሐምሌ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የበረሃ አንበጣ መንጋ እንደሚያሰጋት ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ጎርፍና ድርቅ ለአጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ፈተና በሆኑበት ወቀት የበረሃ አንበጣ መንጋ መከሰት ከፍተኛ ቀውስ እንዳያስከትል ስጋቶች አይለዋል፡፡ የአየር ሁኔታው ለበረሃ አንበጣ መራባት ምቹ መሆንና ረዥም ርቀት ለመብረር አጋዥ የነፋስ ሁኔታ መኖር የበረሃ አንበጣውን ምሥራቅ አፍሪካን እንዲያዳርስና ወደ መጀመሪያ መነሻው የመን ለመድረስ እንደሚረዳውም ተመላክቷል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየኮሮናቫይረስ ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ ተደረገ።
Next articleየባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ ምርመራ ጀመረ፡፡