
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአብዛኞቹ የሀገራችን ከተሞች በተለይም በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ የትራንስፖርት ችግር የተለመደ ነው።
በባሕር ዳር ከተማም ይህ ችግር ይስተዋላል። ስለትራንስፖርት ሲነሳ በታክሲ ላይ ብዙ ገጠመኞች ቢኖሩም ሁሌም የማልረሳው ግን አንድ ነገር አለኝ።
ለማኅበራዊ ጉዳይ ወጣ ብለን ታክሲ እየጠበቅን አንድ ታክሲ ላይ ለመሳፈር ምልክት ስናሳየው አልፎን ሄደ። ሞልቶ ግን አልነበረም። ይልቁንም ከእኛ አለፍ ብለው ከቆሙ ወጣቶች ፊት ሄዶ እነሱን ሲጭን እርመድ እርመድ ብየ ደረስኩበት። ለረዳቱ ምነው አልፈኸን መጣህ እያልኩ ለመሳፈር ስዘጋጅ “አይኾንም” ይለኛል።
አብራኝ የነበረችው እስክትደርስ እየጠበቅኩ ምክንያቱን ስጠይቀው “ሦስተኛ ትርፍ ሰው ለመጫን አይጠጉልኝም’’ ብሎ ትቶን ሄደ። ለካ ወፍራም ሰው ሲጭኑ ትርፍ ሰው ለማስጠጋት ስለማይመች ነበር ትቶን የሄደው።
የታክሲ አገልግሎት ነገር ሲነሳ አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ትርፍ መጫን በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ሕዝቡም ስምምነት የፈረመ ይመስል ተጨናንቆ መጓዝ ባሕል በሚመስል ደረጃ ሁላችንም የምናየው ጉዳይ ነው።
በባሕር ዳር ከተማ ትርፍ ከመጫን ባለፈ በተለይም ጠዋት ከዓባይ ማዶ ገበያ ታክሲ መያዣ እና ምሽት ላይ ከመሀል ከተማ ገበያ ወደ ዓባይ ማዶ፣ ከዋናው ንግድ ባንክ ወደ ቀበሌ 14 የተለያዩ ቦታዎች ለመሄድ ታክሲ ለማግኘት በመጋፋት ሞባይሉ የሚዘረፈው እና ኪሱ በሌባ የሚፈተሸው ብዙ ነው።
ችግሩም የማይቀረፍ መስሎ ተሳፋሪውም አይስተካከልም በሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት የታክሲ ሹፌሮችን እና ረዳቶችን አለፍ ሲልም ሕግ አላስከበሩም ብሎ የሚያስባቸውን የትራፊክ ፖሊሶችን እና የመንገድ ትራንስፖርት ባለሙያዎችን የሚረግመው ሰው ብዙ ነው።
አልፎ አልፎም ለመብታቸው የሚታገሉ ተሳፋሪዎች ‘’ጠጋ በሉ’’ ሲባሉ ‘’አይኾንም’’ የሚሉ ቢኖርም የታክሲ ረዳቶች ግልምጫና ስድብ ሲከፋም ከታክሲ ውረድ መባል አለ፡፡ እንደነዚህ አይነት ዜጎችን ማበረታታት ሲገባ ‘’ምናለ ጠጋ ቢል ለአስር ደቂቃ መንገድ’’ በማለት ሕገ ወጥነትን የሚያበረታቱም ይስተዋላሉ።
ታዲያ የሰሞኑ ትዝብቴ በከተማው በተለይም ዋና ዋና በሚባሉ ታክሲ የሚንቀሳቀስባቸው መስመሮች ለታክሲ የተፈቀደውን 12 ሰው ብቻ ጭኖ ማየቴ አስገርሞኛል። እንደ እውነቱ ከኾነ ነገሩ ትክክለኛ እና መኾን ያለበት ቢኾንም ከ18 ሰው በላይ መጫን እንደ ትክክለኛነት ቆጥረነው ጠጋ በሉ ሳንባል ትርፍ መጫኛ ቦታ ማመቻቸትን በመለማመዳችን ይመስለኛል አግራሞት የፈጠረብኝ።
በከተማዋ ዋና ዋና መስመሮች ታክሲ የሚጠብቀው ማኅበረሰብም ከመጋፋት ይልቅ በሰልፍ ተራውን ጠብቆ በመሳፈር ራሱን ከእንግልት እና ከሌባ ለመጠበቅ ያለው ጅምር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችም ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጭ ሕግ ሲያስከብሩም ታዝቤያለው፡፡
ኾኖም ሕግ አክብሮ መሥራቱ በዋና ዋና መሥመሮች ቢኖርም በውስጥ ለውስጥ መንገዶች እና ትራፊክ ፖሊሶች በሌሉባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም ታክሲዎች እና ባጃጆች ትርፍ ሲጭኑ ይስተዋላል፡፡
ይሁንና ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል? ትራፊኮች መንገድ ላይ እስከቆሙ ድረስ ወይስ ማኅበረሰቡ መብቱን አውቆ አይኾንም ብሎ ለመብቱ ይቆም ይኾን? የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አካላትስ ሕገ ወጥነትን አስወግደው ሕግ አክብረው አገልግሎትን መስጠትን ባሕል ያደርጉት ይኾን?
እንግዲህ ለሁሉም የሚበጀው ሕግ ማክበር በመኾኑ ማኅበረሰቡም ለሕግ አስከባሪዎች ከመተው ይልቅ በራሱ መብቱን ሊያስከበር ይገባል፡፡
አገልግሎት ሰጭዎችም ሕግ በማክበር ለማኅበረሰቡ አገልገሎት መስጠትን ባሕል ማድረግ አለባቸው፡፡ ካልኾነ የአንድ ሰሞን ኾኖ እንዳይቀር ስጋት ቢፈጥርብኝም ከሰሞኑ እየታየ ያለው የትራፊክ ሕግ ማክበር እና ማስከበር ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት እላለሁ፡፡
ዘጋቢ:- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
