“ስፓኒሽ ፍሉ”

8
ባሕር ዳር: ኅዳር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ “ስፓኒሽ ፍሉ” የተሰኘ ወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። የወረርሽኞች ሁሉ “እናት” በሚል የሚጠራው ይህ ወረርሽኝ በሁለት ዓመት ብቻ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ሕይዎት ቀጥፏልም ይባላል።
ያኔ የዓለም ሕዝብ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ነበር። ከሕዝቡ አንድ ሦስተኛው በወረርሽኙ ተይዞ እንደነበር የታሪክ አጥኚዎች ይናገራሉ።
ወረርሽኙ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በላይ ሰዎችን ገድሏል ነው የሚባለው። ያኔ ሳይንስ እንደ ዛሬው አልተራቀቀም ነበር። በሽታ መከላከልም ቀላል አልነበረም።
ሐኪሞች “የኅዳር በሽታ” ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ቢያውቁም፤ የበሽታው መንስኤ ባክቴሪያ እንጂ ቫይረስ መኾኑን አልተገነዘቡም ነበር ይላል ታሪኩ።
ያኔ ዓለም አቀፍ የጤና ሥርዓት ማዕቀፍም አልነበረም። ሀብታም በሚባሉ ሀገራት ሳይቀር የአካባቢ ንጽሕናን መጠበቅ እንደ ቅንጦት ይቆጠር ነበር።
“ስፓኒሽ ፍሉ ዓለምን እንዴት ለወጠ” በሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ፔል ራይደር ያኔ ኢንዱስትሪ በተስፋፋባቸው ሀገራት ሐኪሞች የእራሳቸው ቅጥረኛ ነበሩ ይላሉ። ሐኪሞች በተራድኦ ድርጅቶች ወይም በሃይማኖት ተቋሞችም ይደገፉ ነበር ሲሉ አስፍረዋል።
“የኅዳር በሽታ” ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ነበር ጉዳት ያስከተለው። በብዛት የሞቱት ከ20 እስከ 40 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ አምራቾችም ናቸው።
ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የተመለሱ ወታደሮች ይኖሩበት በነበረ ማቆያ ውስጥ እንደተቀሰቀሰ የሚታመነው ይህ ወረርሽኝ፤ በዋነኛነት ያጠቃው ወንዶችን ነበር። ድሃ ሀገሮችም በግንባር ቀደምነት ተጎድተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አፍሪካ ትጠቀሳለች፡፡
የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ በኢትየጵያ ከኅዳር 07 እስከ 20/1911 ዓ.ም ለ14 ቀናት ገደማ የቆየ እንደ ነበር ይነገራል፡፡ በሽታው በኅዳር ወር የተከሰተ በመኾኑ ሕዝቡ የኅዳር በሽታ እያለ ጠራው ተብሎ ተጽፏል።
ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ወረርሽኙ እስከ 40 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ለሞት ዳርጓል። በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 9 ሺህ ዜጎች በበሽታው ሞተዋል ብለዋል በመጽሐፋቸው፡፡
በተለይም በዚህ ሳምንት ኅዳር 12/1911 ዓ.ም በርካታ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት በመኾኑ በቀኑ የጽዳት ዘመቻ እንዲደረግ በአዋጅ ተነግሮ ስለነበር ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ይህ ነገር እንደ ባሕል ተወስዶ በየዓመቱ ሕዳር 12 ቀን የጽዳት ዘመቻ ይደረግ ጀመር። ይህም በተለምዶ ኅዳር ሲታጠን በሚልም እየተጠራ እስከዛሬ ዘለቀ፡፡
✍️ ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ ሐያሲ እና አርታኢ አማረ ማሞ
በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ በደራሲነት፣ በተርጓሚነት፣ በሐያሲነት እና በአርታኢነት ሥራዎቻቸው በቀዳሚነት ስማቸው ከሚነሱት መካከል አንዱ የኾኑት አንጋፋው ደራሲ፣ ተርጓሚ እና ሐያሲ አማረ ማሞ ይገኙበታል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ፍስሐ ገነት በተባለ መንደር በዚህ ሳምንት ኅዳር 12/1939 ዓ.ም እንደተወለዱ የዕውቅ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦችን ታሪክ የሚከትበው ዘብላክ ላዮን የተሰኘው መጽሔት ይጠቁማል።
ደራሲው ዕድሜያቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት የታተሩ ሰው ስለመኾናቸውም መጽሐፉ ያትታል። በዚህም አማረ ማሞ ከ27 በላይ መጻሕፍትን ለአንባብያን አበርክተዋል።
በአርትኦት እና በሐያሲነት ጭምር አበርክቷቸው የሚጠቀስላቸው ደራሲ አማረ ማሞ የኢትዮጵያ መጻሕፍት ድርጅትን በሥራ አሥኪያጅነት ሲመሩ የነበሩም ናቸው።
ደራሲው ለአንባብያን ካቀረቧቸው መጻሕፍት መካከል እሪ በል ሀገሬ፣ አሳረኛው፣ የዴዜዴራታ ምክር፣ አግብቼሻለሁ እና ሳቅና ቁም ነገር የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።
ደራሲ አማረ ማሞ የቀለም ጠብታ በሚል የኢ ልብወለድ አጻጻፍ መሠረታዊ መመሪያ መጽሐፍ እንዲሁም የልብወለድ ድርሰት አጻጻፍ የሚሉ ተያያዥነት ያላቸው የድርሰት መማሪያ መጻሕፍትንም ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች አጋዥ ይኾኑ ዘንድ ደርሰዋል።
ከስድስት በላይ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ደራሲ፣ አርታኢ እና ተርጓሚ አማረ ማሞ “አሳረኛው” በማለት ወደ አማርኛ የመለሱትን የዝነኛ ደራሲ ነጂብ ማህፉዝን ድርሰት እና ሌሎች ታላላቅ የትርጉም ሥራዎችንም ለአንባቢ አበርክተዋል።
በአርታኢነትም የበዓሉ ግርማ፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ፣ የሙሉጌታ ጉደታን እና የሌሎች በርካታ ደራሲያን ሥራዎችን አርትኦት በመሥራት ሥራዎቻቸው ይበልጥ ተነባቢ እና ተወዳጅ እንዲኾኑ አስችለዋል።
ደራሲ አማረ ማሞ ካበረከቷቸው ሥራዎች መካከል የልጆች ወጥ የድርሰት እና የትርጉም ሥራዎችም የሚጠቀሱ ናቸው።
መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው የትርጉም ሥራዎቻቸውን ለአንባቢያን እንካችሁ ያሉት ደራሲው
የካታኩምቡ ሰማዕት፣ የዋልተር ትሮቢሽ (አግብቼሻለሁ እና አንዲት ወጣት ወድጄ)፣ ማርቲን ሉተር ጥቂቶቹ ሲኾኑ ወደ ሲውዲሽ ቋንቋ የተመለሰላቸው የእውነት ብልጭታዎች የተሰኘ የአጫጭር ልቦለድ ሥብስብ ሥራም አላቸው።
ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል በተለይ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በላቲን ቋንቋ ተጽፎ በእርሳቸው ወደ አማርኛ የተመለሰው “ዴዚ ዴራታ” አሁንም ተወዳጅ ከኾኑ ሥራዎቻቸው ይጠቀሳሉ።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የዕድሜ ልክ የክብር አባል እንደነበሩም ታሪካቸው ይናገራል።
✍️ የጀርመን የመጀመሪያዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል
አንጌላ ሜርክል የጀርመን የመጀመሪያዋ ሴት መራሒተ መንግሥት ኾነው የተሾሙት ኅዳር 13/1998 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር።
ሜርክል ለ16 ዓመታት ያህል የጀርመን መራሒተ መንግሥት ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተው ታኅሣሥ 2014 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ሥልጣናቸውን ለኦላፍ ሾልዝ ለቅቀዋል።
በአውሮፓ ውስጥ ከሩሲያ በመቀጠል በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የኾነችውን ጀርመን ያሥተዳደሩት ሜርክል ሀገራቸው የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገር ውስጥ ጠንካራዋ ደጋፊ እንድትኾንም አስችለዋል፡፡
ሀገራቸው ጀርመን ስደተኞችን ተቀብላ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አለባት በሚል ጠንካራ አቋም የነበራቸው ሜርክል በዚህም በሀገራቸው በሚኖሩ ሌሎች ዜጎች በጥሩ ዕይታ እንዲታዩም አስችሏቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰበቡም በሥልጣን ዘመናቸው በመልካም የሚታዩ ሰውም ናቸው፡፡
ሜርክል በዓለም ላይ ጦርነቶች እንዳይቀሰቀሱ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውም ይነገራል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሠው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ ሀጋራቸው ቀድማ መድረስ አለባት በሚል እሳቤ የሚታወቁት የጀርመን የመጀመሪያዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርከል ይህንንም በተግባር ስለመፈጸማቸው ነው የጀርመን ድምጽ (ዶቸበለ) ከዚህ በፊት ስለ አንጌለ ሜርከል ባወጣው ታሪክ ያስነበበው፡፡
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleየብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀንን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ኾነን ልናከብረው ይገባል።
Next article“‎ጠጋ ጠጋ በሉ”