
አዲስ አበባ፡ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስከረም 18/2018 ዓ.ም ነው ተጠናቅቆ ወደ ሥራ የገባው።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አሥኪያጂ ከበደ ሻሜቦ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሰባት ተቋማትን እና 20 አገልግሎቶችን ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
አስካሁን ለ1ሺህ 948 ተገልጋዮች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት መቻሉን የገለጹት ሥራ አሥኪያጁ በዚህም የተገልጋዩን እርካታ 97 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ስትራቴጂን የሚያግዝ መኾኑን ነው የገለጹት።
በቀጣይም 60 አገልግሎቶችን አካቶ ለመሥራት መታቀዱን ነው ያብራሩት። በክልሉ ሌሎች ከተሞች ለማስፋትም እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ተቋማት ሲሄዱ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት በማስቀረት ጊዜያቸውን እና ወጭአቸውን የሚቆጥብ አገልግሎት በአንድ ማዕከል ውስጥ ማግኘታቸውን ተገልጋዮች ገልጸዋል።
ከፋይል መጥፋት ጋር ተያይዞም ያጋጥም የነበረውን ችግር ዲጂታል በኾነ መንገድ መቅረፍ መቻሉንም ተናግረዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሀገር አቀፍ ኢኒሼቲቭ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች እየተተገበረ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሔም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
