የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ መሥራት ከቻሉ ሰላምን በዘላቂነት ማምጣት ይቻላል።

0

ባሕርዳር፡ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ተግባራት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

ከተማ አሥተዳደሩ “ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ነው ውይይት ያደረገው።

የውይይቱ ተሳታፊ ቀሲስ መላክ መለሰ ከመከባበር ሰላም ስለሚመጣ ትንሹ ትልቁን ማክበር ይገባዋል ብለዋል። ባለማገናዘብ እና ባለማስተዋል ግን በርካታ ችግሮች መፈጠራቸውን ነው የጠቀሱት።

የሃይማኖት አባቶች ልጆችን መምከር እና ማስተማር ከቻሉ በጎ ያልኾኑ ተግባራት እየቀነሱ ሰላም እየጎለበተ ይመጣል ብለዋል። ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለ ሰላም ትናንት ስታስተምር ነበር፤ አሁን ላይም እያስተማረች ነው፤ ቀጣይም ታስተምራለች ነው ያሉት። ማኅበረሰቡም ሃይማኖታዊ አስተምሮን ተቀባይ እንዲኾን አስገንዝበዋል።

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ሐጂ አሊ ሙሐመድ ኑር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢታለፍም በባሕር ዳር ከተማ ትላልቅ የልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። ከተማዋ ሰላማዊ መኾኗንም ገልጸዋል።

ከሃይማኖት አባቶች ብዙ የሚጠበቅ ነገር አለ ያሉት ሐጂ አሊ እየተፈጠረ ላለው ችግር ተጠያቂው የሃይማኖት አባቶች ነን ብለዋል። የሃይማኖት አባቶች አንተም ተው አንተም ተው ማለት ቢችሉ ካለው የሰላም ችግር አይደረስም ነበር ነው ያሉት። ጠላቶቻችን መሳሪያ ያደረጉን ድክመቶቻችን አይተው ነው ብለዋል። በቅርብ ጊዜ ሰላምን መልሶ ወደ ልማት መዞር ይገባል ነው ያሉት።

የባሕር ዳር የሀገር ሽማግሌ አበበ ወንዴ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ለከተማዋ ካላት ውበት በላይ ሌላ ውበት የሚጨምሩ ናቸው፤ ሰላምንም በልማቱ ልክ ዘላቂ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ሰላም የሚመጣውም ኾነ የሚጠፋው እርስ በእርስ በሚኖር የመከባበር ሁኔታ እንደኾነ አስረድተዋል። እርስ በእርስ መወቃቀስን ወደ ጎን ትቶ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ለሰላም መንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል። የሰላም መጥፋት ማኅበረሰቡን በኢኮኖሚ እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ጎድቶታል ነው ያሉት።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰፈር ልጅን ጎረቤት ሲቆጣ ለምን ልጄን ተቆጣህ የሚል ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው፤ ይህ ደግሞ ልጅን ብቻ ሳይኾን ቤተሰብን ከፍ ብሎም ሀገርን ይጎዳል ብለዋል። ኢትዮጵያዊ እሴት ይህ አይደለም፤ መካሪ እና ዘካሪ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

የተፈጠረውን ወቅታዊ ጉዳይ በመጠቀም በዝርፊያ እና እገታ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችንም በጋራ መታገል እንደሚገባም ተናግረዋል። ማኅበረሰቡን ከስጋት ለማውጣት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና መላው ማኅበረሰብ በጋራ መሥራት ከቻሉ ሰላምን በዘላቂነት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ላለፉት ሁለት ዓመታት ገጥሞ በነበረ የሰላም ችግር ዙሪያ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻለ ሰላም መፈጠሩን ተናግረዋል። ይህን ደግሞ በዘላቂነት ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት።

ሰላምን በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችንም የበለጠ ማጠናከር ፣ ማስፋት እና በፍጥነት መፈጸም እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን፣ የሰላም ጠንቅ የኾኑ ጉዳዮችን በመፍታት ሁለንተናዊ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን አጠናክሮ ለመቀጠል የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአባቶች የቆዩ የኢትዮጵያ እሴቶችን ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
Next articleሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮችን ከእንግልት እየታገደ ነው።