አባቶች የቆዩ የኢትዮጵያ እሴቶችን ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

1

ጎንደር: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ከወገራ ወረዳ እና ከአምባ ጊዮርጊስ ከተማ አሥተዳደር ከተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በዘላቂ ሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

‎ውይይቱ በሁለቱም አሥተዳደሮች ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ያለመ ነው።

‎የውይይቱ ተሳታፊዎች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። አሁን ላይ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን እና ለዘላቂ ሰላም እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የሰላም መነሻው ውይይት በመኾኑ መፍትሔ የሚያመጡ ንግግሮች ላይ አተኮሮ መነጋገር ያስፈልጋል ብለዋል።

‎እየሞተ፣ እየተፈናቀለ፣ እየወደመ ያለው የራስ ወገን እና ሃብት ነው ያሉት ተሳታፊዎች ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታትን ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የወገራ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ተወካይ እና የመሬት ጽሕፈት ቤት ኀለፊ አይፈራም አያናው የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲመርጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

‎አባቶች አባታዊ ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

‎የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ፋሲል ሰንደቁ “ኢትዮጵያ በጦርነት እንድትቀጥል በሚሠሩ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራ እንዳንጠለፍ መሥራት ያስፈልጋል” ብለዋል።

‎ለዜጎች የተመቸች ሀገር ለመፍጠር እየተሠራ ያለውን የሰላም ተግባር ኀብረተሰቡ እንዲያግዝም ጠይቀዋል።

‎ከባሕል ያፈነገጠ እገታ እና ዝርፊያን ለማስቀረት የጋራ ሥራ እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

‎መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ አላጠፈም ያሉት ኀላፊው በሰላም ወደ ሕዝብ ለሚመጡ የታጠቁ ኀይሎች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስታውቀዋል።

በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል እዘዘው መኮነን አባቶች የቆዩ የኢትዮጵያ እሴቶችን ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

‎የእረስ በእርስ ጦርነት ሀገር እና ሕዝብን የሚጎዳ በመኾኑ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የተሰጣቸውን ጸጋ በአግባቡ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ.ር) ጋር ተወያዩ።
Next articleየሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ መሥራት ከቻሉ ሰላምን በዘላቂነት ማምጣት ይቻላል።