
ደሴ: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ አሥተዳደር ”ዘካሪ፣ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ከደሴ ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የሰላምን ዋጋ በአጽንኦት በመረዳት የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሰሚነታችሁን በመጠቀም ለሰላም መጽናት የበኩላችሁን ሚና ልትወጡ ይገባል ብለዋል።
ውስጣዊ ሰላምን እና አንድነትን በማጠናከር ሀገሪቱን ከባሕር በር ለማግለል የተሠራውን ኢ ምክንያታዊ ሁኔታ በተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ትግል መፍታት እንደሚገባም አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አዝመራ ማስረሻ በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ኀብረተሰቡን እየመከሩ እና እያረሙ አብሮነቱን እንዲያጠናከር ብዙ ሚና መጫዎታቸውን ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም በግለሰቦች እና በማኀበረሰብ መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ችግሮችን ለመፍታት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን ለማርጋገጥ በሚደረገው ጥረት ለባሕላዊ የግጭት አፈታት ትኩረት መሰጠት እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
