ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

0

አዲስ አበባ: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን ወይም የነጭ ሪቫን ቀን ዓመታዊ የንቅናቄ መርሐ ግብርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) ጾታን መሠረት ያደረገ አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የሚያስከትል ጥቃት የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኾኑን ተናግረዋል። በግልም ኾነ በማኅበራዊ ሕይዎት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር ድርጊት መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ ድርጊት በዓለም አቀፍ እና በኢትዮጵያ ሕጎች የተረጋገጡ መሠረታዊ ነጻነቶች እና መብቶችን የሚጥስ እንደኾነም ተናግረዋል። በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃት አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ደኅንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር፣ ሙያዊ እድገታቸው እና ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያዳክም ነው ብለዋል።

ጥቃቱ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በሀገር ላይ መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በማስከተል ዘላቂ ልማት እንዳይረጋገጥ እንቅፋት የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ አሠራሮችን እና የአገልግሎት ሥርዓትን በመዘርጋት እየሠራ ነው ብለዋል። በተጎጅዎች ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ የማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና የሕግ ምላሽ ክፍተቶችን ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዓለም አቀፍ የፀረ ጾታ ጥቃት ቀንን ከኅዳር 16 እስከ 30/2018 ዓ.ም ድረስ ለ16 ለማክበር በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የፀረ ጾታዊ ጥቃት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እንደሚከበርም አስታውቀዋል።

“ጥቃትን የማይታገስ ማኅበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ከኅዳር 16 እስከ 30/2018 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው መርሐ ግብር ኅብረተሰቡ ጥቃትን ያለመታገስ አቋም በሚያሳይበት መንገድ ይከበራል ብለዋል።

የንቅናቄው ዓላማ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ ለተጎጂዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እና በመንግሥት የተያዙ ዕቅዶችን ተግባራዊ በማድረግ መላው ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ ጥቃትን እንዲወገድ ለማድረግ መኾኑንም ገልጸዋል።

ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል በሀገራዊ የንቅናቄ ሰነዱ ዙሪያ ለ55 ሚሊዮን የማኅበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ዘዴዎች ግንዛቤ ይፈጠራል ነው ያሉት።

በቴክኖሎጂ አማካኝነት የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ግንዛቤ ለማፍጠር የሚያስችል መመሪያ በማዘጋጀት ለሁሉም ባለደርሻ አካላት ተደራሽ ማድረግ እና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመድኃኒት የተላመደ በሽታ የማኅበረሰብ ስጋት እየኾነ ነው።