መድኃኒት የተላመደ በሽታ የማኅበረሰብ ስጋት እየኾነ ነው።

3

ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ መድኃኒት የተለማመዱ ጀርሞችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

እ.ኤ.አ 2050 መድኃኒቱን በተላመደ ጀርም አማካኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ 10 ሚሊዩን የሚጠጉ ዜጎች ሕይዎታቸውን ያጣሉ ተብሎ ይገመታል።

ይህንን አስመልክቶ የዓለም አቀፍ የመድኃኒት ብግርነት የግንዛቤ ሳምንት ተብሎ አየተከበረ ነው። ሳምንቱ “አሁን እንተግብር፣ ዛሬን እንከላከል እና ነገን አስተማማኝ ደኅንነትን እንፍጠር” በሚል መሪ መልዕክት ነው እየተከበረ የሚገኘው።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ መድኃኒት የተላመደ ፀረ ተህዋሲያን በሽታ ከፍተኛ ስጋት እየኾነ መጥቷል ብለዋል።

መድኃኒቶች ተህዋሲያንን መግደል፣ መቆጣጠር ወይም መራባታቸውን መግታት ሲሳናቸው መድኃኒቶች በደም ውስጥ ቢኖሩም ተህዋሲያኑ መራባት ይችላሉ ነው ያሉት።

በቀጣይ ማንኛውም የሚመለከተው አካል ስለ ጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል ነው ያሉት።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) መድኃኒት የተላመደ ፀረ ተህዋሲያን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሕይዎት እያሳጣ ነው ብለዋል። ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ ችግር እየኾነ በመምጣቱ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ፀረ ተህዋሲያን የሁሉም የጤና ችግሮች እየኾኑ መምጣታቸውንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥትም መድኃኒት የተላመዱ ፀረ ተህዋሲያን በሽታዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወንድም በወንድሙ ላይ መዝመት ከአማራ ሕዝብ እሴት ያፈነገጠ ነው።
Next articleጥቃትን ለመከላከል እና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።