ወንድም በወንድሙ ላይ መዝመት ከአማራ ሕዝብ እሴት ያፈነገጠ ነው።

0

ደብረ ብርሃን: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር “ዘካሪ መካሪ የሀገር ሽማግሌ እና የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

የውይይቱ ዓላማ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲጸና የሃይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማስቻል ነው።

ውይይቱን ያስጀመሩት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት የሰላም እጦት የከተማዋን ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለዋል።

በከተማዋ እየተስተዋሉ ያሉ የእገታ፣ የዝርፊያ እና መሰል የወንጀል ድርጊቶች እድገት እያቀጨጩ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህንን አሳሳቢ ችግር የመላመድ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ እንደኾነም ጠቁመዋል።

መንግሥት ይህንን ችግር በጸጥታ መዋቅሩ አማካኝነት የሕዝቡን ሰላም ለማስከበር ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል አቶ በድሉ።

ይሁን እንጂ መንግሥት በጸጥታ ኃይል ብቻ ሰላምን ሊያመጣ አይችልም ያሉት አቶ በድሉ ሕዝቡ የሰላም ዘብ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለይ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሰላምን የማጽናት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በውይይቱ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በአማራ ክልል የተፈጠረው ጦርነት ሕዝቡን አሁንም ለከፍተኛ ችግር እያጋለጠው ይገኛል ብለዋል።

“ወንድም ወንድሙን በመግደሉ የማይቆጭበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ያሉት ተሳታፊዎቹ ይህም ከአማራ ሕዝብ እሴት ያፈነገጠ መኾኑን አንስተዋል።

ብልሀት የታከለበት የአመራር ጥበብን በመጠቀም ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ መንግሥት በሆደ ሰፊነት አተያይ ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ የሰጠውን አቅጣጫ አጠናክሮ እዲቀጥልም ጠይቀዋል።

ውይይት የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ በተለይ የታጠቁትን በማወያየት ሕዝቡን ከዘርፈ ብዙ ውድመቶች መታደግ ይቻላል ብለዋል።

እንደ ሀገር የሕዝቡን ረፍት የነሱ ግጭቶች በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሚደገፉ መኾኑን ያነሱት ተሳታፊዎቹ ተባብረን የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ መንጠቅ አለብን ነው ያሉት።

በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሙስና እና ብልሹ አሠራር እየተስፋፋ በሕዝብ እና በመንግሥት መካከልም ክፍተት እየተፈጠረ ነው ብለዋል። ይህን ከተማ አሥተዳደሩ በአስቸኳይ ሊያስቆም እንደሚገባም በተሳታፊዎች ተነስቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article260 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።