
በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።
በማሻሻያው መሠረት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማኅበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም ተፈቅዷል።
ይህም ከዚህ ቀደም የአስክሬን የላብራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ መሻሻሉን ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በቀብር ሥፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን ማከሄድ አለባቸው የሚለው መመሪያው አልተሻሻለም ብለዋል።
ግለሰቦች በኮሮናቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግሏቸው የቤተሰብ አባላትና የራሳቸው ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተፈጻሚ የሚሆን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የግለሰቦችን የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት አግባብ ከሆነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረጉም ተገልጿል።
ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በተለይም ወደ አገር ከገቡ በኋላ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት አገር ተመርምረው ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ ናሙና ተወስዶ በቤታቸወ 14 ቀናት እንዲቆዩ ይደረጋልም ተብሏል።
ኢዜአ እንደዘገበው ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ሪፖርት ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ እንደሚደረግ ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
ይህም ከዚህ ቀደም ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ ለ7 ቀናት ብቻ እንዲሆን ተወስኗል።
