
ባሕር ዳር: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት ለ1 ሚሊዮን 96 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ነው።
ባለፉት 4 ወራት 260 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የአማራ ክልል ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አወቀ ዘመነ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ ለ187 ሺህ የሚኾኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው ብለዋል። የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ዜጎችም የመሬት አቅርቦት፣ የሼድ አቅርቦት፣ የብድር አቅርቦት እና የገበያ ትስስር ድጋፍ እንደ ተደረገላቸው ምክትል ኀላፊው አንስተዋል።
ከ16 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች እና ከ41 ሺህ በላይ አንቀሳቃሾች የብድር ተጠቃሚ መኾናቸውንም አቶ አወቀ ጠቅሰዋል።
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጎች የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መንግሥት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት መያዙን ምክትል ኀላፊው ገልጸዋል።
ባለፉት 4 ወራትም ወደ 39 ሺህ የሚደርሱ ኢንተርፕራይዞች የዕድሉ ተጠቃሚ መኾናቸውም ተነስቷል። ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ለገበያ ትስስር ሥራ መዋሉንም አቶ አወቀ ተናግረዋል።
100 ሺህ ዜጎችን የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ወደ 6 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መኾናቸውንም ምክትል ኀላፊው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
