
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር “ዘካሪ መካሪ የሀገር ሽምግልና፣ የሃይማኖት አባት ለዘላቂ ሰላም እና ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ተግባራት ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፋት ሁለት ዓመታት ክልሉ ከገጠመው ችግር በማውጣት ሰላምን ለማምጣት የባሕር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የነበራቸው አበርክቶ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
አሁን ላይም የገጠመው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ሄዶ በከተማዋ ሰላምን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይም ከተማዋ ከአቻ ከተሞች ጋር ብቻ ሳይኾን ከሌሎች ዓለም ሀገራት ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትኾን ሰላም እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ ሰላምን ዳግም ማጣት የለብንም ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ መንግሥት እንደ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶች እንደ ሃይማኖት አባት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንደ ሀገር ሽማግሌ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ከተማ ነዋሪ በትብብር የድርሻችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
