ሥራውን በዕውቀት የሚፈጽም የመንግሥት ሠራተኛ በሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች መፈጠር አለበት።

1

ደብረ ብርሃን: ኅዳር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳደር” አገልጋይ እና የሰላም ዘብ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት የመንግሥት ሠራተኞች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ መካሻ አለማየሁ የዞኑ መንግሥት ሠራተኞች የአገልጋይነትን መንፈስ ተላብሰው በመሥራት ረገድ ያሏቸውን መልካም ልምዶች አጠናክረው ማስቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

በክልል ደረጃ በተደረገ ምዘና ባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸማቸው የዞኑ 25 መምሪያዎች ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ማሳያ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው አንስተዋል፡፡

ይህንን ልምድ በመቀመር በበጀት ዓመቱም አጠናክሮ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መሠራት አለበት ብለዋል አቶ መካሻ፡፡

የተቋምን ተልዕኮ በሚገባ የተረዳ፣ አገልጋይ እና ሥራውን በዕውቀት የሚሠራ የመንግሥት ሠራተኛ በሁሉም መሥሪያ ቤቶች መፈጠር አለበት ነው ያሉት፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኤልያስ አበበ የዞኑ መንግሥት ሠራተኞች ጠንካራ የሥራ ባሕልን የገነቡ፣ ውጤታማ እና ተቀራራቢ የመፈጸም አቅምን ያዳበሩ መኾን እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር እድገትን በማስመዝገብ እና ድህነትን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት የመንግሥት ሠራተኞች ጉልህ ድርሻ ያላቸው መኾኑን አቶ ኤሊያስ ተናግረዋል፡፡

ቅንነትን የተላበሰ አገልግሎት መስጠት፣ ለሰላም እሴት መጎልበት አበርክቶን ማዋጣት እና ቀጣይነት ላለው ለውጥ ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ አይነኩሉ አበበ በሁሉም መምሪያዎች ጥራት ያለው ዕቅድ በማቀድ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የሚሰጡ ተልዕኮዎችን ተቀብሎ በመሥራት ተገቢ አገልግሎት በመስጠት ረገድ በሩብ ዓመቱ አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይ ወጥነት ባለው መንገድ ሰላም እንዲሰፍን የመንግሥት ሠራተኞች ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ:- ገንዘብ ታደሰ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተወያዩ።
Next articleየሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለሰላም የነበራቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነበር።