
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) የውድድሮች መቋረጥ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ እና የመፍትሔ ሐሳቦችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
የአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ልጆች ዋልያዎቹ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ስም ያላትን ኮትዲቯር ካሸነፉ በኋላ በመልካም መነቃቃት ላይ ነበሩ፡፡ በግዙፉ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዬም በተደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ “ኮትዲቯር በሰፊ ግብ ልዩነት ታሸንፋለች” የሚለው ግምት የብዙዎች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወጥ አቋም አለመመልከት ኢትዮጵያውያንን ደጋፊዎች ተስፋ ማሳጣቱ ነበር በሀገር ላይ ሽንፈትን ያስመኘው፡፡
ጨዋታው ተጀመረ፤ እንደምታሸንፍ ቅድመ ግምት የተሰጣት ኮትዲቯር በግብ ቀዳሚ ሆነች፤ አስቀድሞ “ስንት ግብ ይቆጠርብናል?” ሲል የነበረው ደጋፊ አንድ ብሎ መቁጠር ጀመረ፡፡ ነገር ግን ነገሩን ሁሉ ፉርሽ ያደረገና አይቮሪኮሳታውያንን አንገት ያስደፋ ውጤት ተመዘገበ፡፡ ጨዋታው በዋልያዎቹ አሸናፊነት ተጠናቅቆ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩ ባንዲራ በድል ተውለበለበ፡፡ “ድሌ ማታ ነው ድሌ” ተጨፈረ፡፡
ኢትዮጵያ ከምድቧ ታላቋን ማሸነፏ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረች ተነገረላት፡፡ ሌሎቹ ተጋጣሚዎቿ ማዳጋስካርና ኒጄር በአንጻሩ እግር ኳሳቸው እንደሌሎቹ ኃያል አለመሆን ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል እንደሆነም እንዲሁ ተነሳ፡፡ በእርግጥ ደሴቲቷ ሀገር ማዳጋስካር በ2019 (እ.አ.አ) የግብፁ የአፍሪካ ዋንጫ የውድድሩ ክስተት መሆን ኢትዮጵያን እንደምትፈትናት መገመት ይቻላል፡፡
የኮሮናቫይረስ ካሸመደመዳቸው ዘርፎች አንዱ እግር ኳስ ነው፡፡ የሚሊዮኖች መዝናኛ፣ እንጀራና ሕይወት የሆነው እግር ኳስ ሲቋረጥ ብዙዎች ተከፍተዋል፡፡ በእርግጥ ከፈረንሳይ ሊግ ውጭ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ወደ ውድድር ተመልሰዋል፡፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሁሉም የሊግ ውድድሮች ያለአሸናፊ ተሰርዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሊግ ውድድር መቋረጥ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ “ውድደሩ እንኳን ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እየተካሄደም በየመካከሉ መቆራረጥ ስለነበር ተፅዕኖው ከፍ ያለ ነበር” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ሀገሮች አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው በአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ በመሆኑ ልምምድም፣ ውድድርም እያደረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ማዳጋስካርም ልምምድ እያደረገች መሆኑን በመግለጽ በኢትዮጵያ ውድድር ስለሌለ የሚሠራው ሥራ ደካማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተጫዋቾችን ብቃት ለመጠበቅ በአውሮፓ ሀገራት የሚተገበሩ ልምምዶችን በሉሲዎቹና በዋሊያዎቹ ላይ ለመተግበር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ተሞክሮው በብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ላይ ውጤታማነቱ ታይቶ ወደ ሊግ ተጫዋቾችም እንደሚወርድ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ወቅት ተጫዋቾች በግል ልምምድ መሥራት እንዳለባቸው አሰልጣኙ መክረዋል፡፡ አሰልጣኞችም ከተጫዋቾች ጋር የሚገናኙበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባ ነው የተናሩት፡፡ እንደ አሰልጣኝ አብርሃም አስተያየት ውድድሮች በመሰረዛቸው በየጨዋታዎች እየተዘዋወሩ ተጫዋቾችን መመልከት አልተቻለም፤ የነበራቸውን ልምድ በመጠቀም በተለያዩ ቦታዎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በብዛት መምረጥና ከስልጠና በኋላ ምርጦችን የመምረጥ ሥራ እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ እግር ኳሱ ላይ ተፅዕኖው ከፍ እንዳይል በየክልሉ ያሉ ታዳጊዎችን በየአሰልጣኞቻቸው ድጋፍ የግል ልምምዶችን ማሠራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች የቪዲዮ ስልጠና መስጠቱን አሰልጣኙ ጠቅሰዋል፤ በውጭ የሚኖሩ አሰልጣኞችም ለኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ልምዳቸውን እያካፈሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) እግር ኳሱ እንዴት መመራት እንዳለበት የሚያሳውቅ ደብዳቤ ለየሀገራቱ እንደሚልክም አስታውቀዋል፡፡ ተጫዋቾች ነገን በተስፋ በመጠበቅ የግል ልምምዳቸውን በመሥራት በአካል ብቃትና በሥነ ልቦና ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ፎቶ፦ ከድረገጽ
