
ጎንደር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሠርተው የማይደክሙ እና ክንደ ብርቱ ጥበበኛ ሰው ናቸው። ከጥበበኞች የቀሰሙትን ልምድ በመጠቀም እና ምርቶችን በመሠብሠብ በመጦሪያ ዕድሜያቸው ለሌሎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
እኒህ ባለ ብርቱ ክንድ የ78 ዓመት አዛውንት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ይገኛሉ።
እርጅና መጣሁ ሲላቸው አልሸነፍ ባይነትን ተላብሰው በ78 ዓመታቸው የንብ ማነብ ሥራን በማከናወን የማር ምርት ያቀርባሉ።
እድሜ ቁጥር ነው የሚሉት አዛውንቱ ጠንክሮ መሥራት፣ በብልሃት ሥራን ማከናወን፣ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ እና ሥራን በወቅቱ መከወን በመቻላቸው በ78 ዓመታቸው ደስተኛ እንዲኾኑ እና የጠራ ንጹሕ ማር ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ ዕድል እንደፈጠረላቸው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ድጋፍ በሚፈልጉበት እድሜያቸው ያልከዷቸው ብርቱ እጆቻቸው በምርታቸው ውጤታማ እንዲኾኑ አድርጓቸዋል።
አቶ እሸቴ አቸነፈ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በንብ ማነብ ሥራ ላይ ይገኛሉ። 95 የንብ ቀፎዎችን በመጠቀም ማርን እያመረቱ ነው። እኒህ አዛውት በ78 ዓመታቸው ለስምንት ልጆቻቸው የሥራ ዕድልን ፈጥረዋል። በዚህም ይበልጥ ደስተኛ መኾናቸውን ነው ያጫወቱን።
በባለፈው ዓመት ከ200 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። በዘንድሮው ዓመት ከ400 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ለማግኘት እየተጉ መኾኑንም አንስተውልናል። ቤተሰቦቻቸውን ከማሥተዳደር አልፎ ቤት በመሥራት እና በሌሎችም ተጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
እድሜ ያልገደባቸው ብርቱው አዛውንት አቶ እሸቴ ውጤታማ ለመኾን ጠንክሮ መሥራት የስኬታቸው ምንጭ መኾኑን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ያገኙትን እውቀት ለሌሎች በማካፈል ለሥራ እንዲተጉ የሕይዎት ተሞክሯቸውን ያጋራሉ።
በደባርቅ ከተማ ከ4 ሺህ 600 በላይ የንብ መንጋዎች እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የከተማ አሥተዳደሩ እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መላኩ ገብረ ሥላሴ ናቸው።
በ2017 ዓ.ም 75 ቶን የማር ምርት መገኘቱን አስታውሰዋል።18 ኢንተርፕራይዞች በንብ ማነብ ሥራ ላይ ተሠማርተው እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በዘርፉ የተሠማሩ አልሚዎች የዘመናዊ ቀፎ ተጠቃሚ እንዲኾኑ መሠራቱንም ገልጸዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 97 የዘመናዊ ቀፎዎችን ለተጠቃዎች ማቅረብ ተችሏል ነው ያሉት።
90 ቶን የማር ምርት ለማግኘት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
