
ገንዳ ውኃ: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን “አገልጋይ እና የሰላም ዘብ የኾነ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለተናዊ እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በገንዳ ውኃ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እያሱ ይላቅ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ማኅበረሰቡን ፍትሐዊ በኾነ መልኩ ማገልገል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የተዛቡ መልዕክቶችን በመመከት ለሀገር ሰላም እና ለሕዝብ ደኅንነት ሊሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሚዛናዊ በመኾን የሰላምን እና የልማትን ሥራዎችን በማጠናከር አጋዥ መኾን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራት የማኅበረሰቡን የመልካም አሥተዳደር ችግር መፍታት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።
ፍትሐዊ አገልገሎት በመስጠት ሰላም እንዲጸና እና ልማት እንዲፋጠን የመንግሥት ሠራተኞች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ሥልጡን እና አገልጋይ የኾነ የሰው ኀይል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በቀጣይ የሚጋጥሙ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በመለየት በፍጥነት ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እንዳለው ማሩ የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መከበር ዘብ በመኾን ለሁለተናዊ ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ በመወጣት ማኅበረሰቡን በቅንነት እና በግልጸኝነት ለማገልገል ጠንክረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ብልሹ አሠራርን ለመቅረፍ መንግሥት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ሕግን ማስከበር አለበትም ብለዋል።
ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ስለማይመጣ የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
