
ደብረ ታቦር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “አገልጋይ እና የሰላም ዘብ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
ከጠቅላላ የመንግሥት ሠራተኛው ጋር ስለ አገልግሎት አሰጣጥ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ነው ወይይት የተካሄደው።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ሰነድ ቀርቦ በተሣታፊዎች ሃሣብ እና አስተያየት ተሰጥቶበታል።
በከተማ አሥተዳደሩ የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራቶች በመንግሥት ሠራተኞች የላቀ አፈጻጸም የተመዘገቡ እንደኾኑ ተነስቷል።
በአንጻሩ የአገልጋይነትን መንፈስ ያለመላበስ እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም አተገባበር ላይ መሠረታዊ ችግሮች በመንግሥት ሠራተኞች ላይ እንደነበሩም በመድረኩ ተመላክቷል።
የተነሱትን ተግዳሮቶችን ለመፍታት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን፣ በጊዜ እና በሰዓት መሥራት ብሎም ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ ተገልጿል።
የመንግሥት ሠራተኞች የአገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ እና የተገልጋይን እርካታን ማሳደግ የቀን ተቀን ተግባራቸው ሊኾን እንደሚገባ ነው የተብራራው።
ተቋማት ለማኅበረሰቡ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች ያለባቸውን ትልቅ ኀላፊነት በመረዳት በታማኝነት እና በቁርጠኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን ባለፉት ዓመታት ያልተሳኩ ጉዳዮችን በቁጭት መሥራት እና መልካም አሥተዳደርን ማስፈን ከመንግሥት ሠራተኛው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዴሴ መኮነን ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለመመለስ እና የመንግሥት ሠራተኛው የሰላም ዘብነቱን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል ዓላማ ያደረገ የውይይት መድረክ መኾኑን አስገንዝበዋል።
የመንግሥት ሠራተኛው ማኅበረሰቡን በቀናነት ማገልገል እንደሚገባው በውል በመረዳት ለማኅበረሰቡ አገልገልግሎት መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ መኾኑን በመገንዘብ ለዚሁም ጠንክሮ መሥራት ወሳኝ እንደኾነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
