
ጎንደር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ”አገልጋይነት እና የሰላም ዘብ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ እምርታ” በሚል ሀሳብ በጎንደር ከተማ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ተካሂዷል ።
ውይይቱ ሰላም እንዲረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኞች የድርሻቸውን መወጣት ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ነው።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጃለም የሀገር ሰላም ለአንድ አካል የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለዋል።
ሁሉም ዜጋ የሰላም ባለቤት በመኾን ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ሀገርን ገንብቶ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባው ተናግረዋል።
መንግሥት ለሀገር ልማት በሰጠው ትኩረት ጎንደር ከተማ ተጠቃሚ መኾኗን የጠቀሱት አቶ ግርማይ የመንግሥት ሠራተኞችም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ኀላፊነት ወስደው የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።።
አገልጋይነት ለሰላም የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት በተገልጋዮች በኩል የሚነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ እንከኖችን በመፍታት ጠንካራ የሥራ ባሕልን ማዳበር እንደሚባም አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች የጸጥታ ችግሩ ዜጎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮቻቸውን በተገቢው መንገድ እንዳይከውኑ አድርጎ መቆየቱን አንስተዋል። አሁን ላይ በከተማዋ ያለውን ሰላም በመጠቀም ከመንግሥት እና ከሕዝብ የተሰጣቸውን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ሰላም እና ልማቷ የተረጋገጠ ሀገርን ለትውልድ ለማስረከብ በባለቤትነት ስሜት መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
