
ፍኖተሰላም: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን አሥተዳደር ከጃቢ ጠህናን ወረዳ እና ከፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የመድረኩ ተሳታፊዎች ባለው የሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት በመራቃቸው ለተለያዩ እንግልቶች መጋለጣቸውን ገልጸዋል።
የተወሰኑ ተማሪዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው ርቀው በመማራቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን ጠቁመዋል።
እርስ በእርስ የሚካሄደው ግጭት ክልሉን ወደ ኋላ እየጎተተው መኾኑን ነው ያብራሩት።
ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትም የሃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስረድተዋል።
መንግሥት አሁንም የሰላም አማራጮችን በማጠናከር ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይ ዓለሙ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ኅብረተሰቡ ለአላስፈላጊ እንግልት መዳረጉን ገልጸዋል።
የልማት ሥራዎችንም ለማከናወን የሰላም እጦቱ ፈታኝ እንዳደረገው አንስተዋል።
ለዚህም ኅብረተሰቡ የሰላም ዘብ በመኾን መታገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል። አሁንም የመንግሥት የሰላም አማራጩ ክፍት መኾኑን አስረድተዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜ ዓለም አንተነህ የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖት ተቋማት ስለሰላም ከመስበክ ባሻገር የታጠቁ ኀይሎች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው አንስተዋል።
መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው ኅብረተሰቡም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሰላም ሁኔታውን ከማረጋጋት በሻገር ከኅብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መኾኑንም ገልጸዋል።
በተለይ ማኅበረሰቡን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋርጠው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
