
ጎንደር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ”አገልጋይ እና የሰላም ዘብ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ ዕምርታ” በሚል መሪ መልዕክት ውይይት እየተካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን ተናግረዋል። የመንግሥት ሠራተኞች አሁን እየመጣ ላለው የሰላም መስፈን እያበረከቱት ያለው ድርሻ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡ አካባቢውን ተደራጅቶ ከመጠበቅ ጀምሮ ተደናግረው ወደ ጫካ የወጡትም ግለሰቦች የሰላምን መንገድ ተከትለው እንዲመለሱ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
እየታየ ባለው የሰላም ተስፋ በዚህ ዓመት በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ መቻላቸውንም ገልጸዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች በዋነኝነት የቆሙበትን ዓላማ በማሳካት ሕዝብ የሚጠይቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ የራሳቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ለሰላም መዘመር፣ ለሕዝብ መቆርቆር፣ የታቀደውን ዕቅድ ማሳካት፣ የዞኑን ማኅበረሰብ ሕይዎት መቀየር እና ወደ ወረዳዎች ተንቀሳቅሶ መደገፍ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ የፓለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ካሳው ንጉሤ ባለፋት ዓመታት ተከስቶ በቆየው የሰላም መደፍረስ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ መሠረተ ልማቶች የቆሙበት፣ ቱሪዝም በክልሉ የተዳከመበት፣ የኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ እና ውድ የኾነው የሰው ሕይወት የተቀጠፈበት መኾኑን ተናግረዋል።
ችግሩንም ለመቅረፍ ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በተደረገው የሕዝብ ምክክርም ከአለፋት ዓመታት በተሻለ ለውጥ መምጣት መጀመሩን እና ሕዝብ ተደራጅቶ ሰላሙን የማስከበር ሥራ እየሠራ መኾኑም ተገልጿል።
በምክክሩ የተሳተፉ የመንግሥት ሠራተኞች ሰላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን እየተወጡ መኾኑን ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
እንደየ ሙያቸው የሥራ ባህሪ ተገልጋይን ማርካት፣ ውጤት መገኘቱን ማረጋገጥ፣ ተለምዷዊ አሠራርን ወደ ዘመናዊነት ማሻገር፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነትን ማረጋገጥ የቀጣይ ትኩረታቸው እንደሚኾንም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፦ዳንኤል ወርቄ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
