ዶክተር አንዷለም ዳኜ ላይ የመግደል ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነበት።

1
ተከሳሽ እሱባለው (ሳሙኤል) ነበረ የተባለው ግለሰብ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡00 – 2፡00 በሚሆንበት ጊዜ ባሕርዳር ከተማ ሰባታሚት ቀበሌ ልዩ ስሙ ቆሼ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሄድ በሰዓቱ ከባሕርዳር ከተማ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረውን ዶክተር አንዷለም ዳኜን የያዘውን ንብረት ለመውሰድ እንዲመቻቸው በማሰብ ያሽከረክር የነበረውን መኪና እንዲያቆም ሲጠይቁት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ሁለት ጥይት በመተኮስ ዶ.ር አንዷለም ዳኜን ደረቱን እና ክንዱን በመምታት የገደሉት በመሆኑ፣ የወ/ህጉን አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 663(2) እና 671(2) የተመለከተውን በመተላለፍ በፈጸመው የከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ ተከሷል ወይንም በአማራጭ የወ/ህጉን አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 539(1)(ሐ) የተመለከተውን በመተላለፍ የመግደል ወንጀል ፈጽሟል የሚል የመጀመሪያ ክስ፣ የወ/ህጉን አንቀጽ 32(1)(ሀ)፣ 27(1) እና 539(1)(ሐ) ላይ የተመለከተውን ተላልፏል በሚል በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ላይ ወደ ጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሄድ የነበረው ዶ.ር በረከት አማረ ላይ ሁለት ጥይት በመተኮስ የመኪናውን ቦዲ በመምታት ተበዳዩን የሳተው በመሆኑ በፈጸመው ከባድ የሆነ ሰው መግደል ሙከራ ወንጀል ተከሷል የሚል ሁለተኛ ክስ፣ እንዲሁም በሶስተኛ ክስ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(3) ላይ የተመለከተውን ተላልፎ ሀሰተኛ የቀበሌ መታወቂያ ሰነዶችን መገልገል ወንጀል ፈጽሟል በሚል በሰሜን ጎጃም ዞን ፍትሕ መምሪያ ክሶች ቀርበውበታል፡፡
ተከሳሹም የቀረቡበትን ክሶች ክዶ የተከራከረ ቢሆንም፣ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የባሕርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዐ/ህግን ማስረጃዎች በመስማት ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ሰጥቶ የመከላከያ ማስረጃዎችን ከሰማ በኋላ ተከሳሹ የቀረቡበትን ክሶች ለመካለከል ባለመቻሉ በ1ኛው ክስ ስር በወ/ህግ አንቀጽ 671(2) ስ፣ በ2ኛው ክስ በወ/ህግ አንቀጽ 27(1) እና 671(1)(ሐ) ስር፣ እንዲሁም በሶስተኛው ክስ በወ/ህጉ አንቀጽ 378 ስር ድንጋጌዎችን በመቀየር የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶ፣ የቅጣት አስተያየቶችን በመመርመር ተከሳሹ በአጠቃላይ በ25 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በሙሉ ድምጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
መረጃው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው
Previous articleየከተማዋን ዘላቂ ሰላም በጋራ በማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን መደገፍ ያስፈልጋል።
Next articleዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተካሄዱ የሚገኙ ሕዝባዊ ውይይቶች አወንታዊ ለውጥ እያስገኙ ነው።