
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ”አገልጋይ እና የሰላም ዘብ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ እመርታ” በሚል መሪ መልዕክት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር እየተወያየ ነው።
የአሥተዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችም በወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ዙሪያ መክረዋል።
ውይይቱን የከፈቱት በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳርከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን በከተማ አሥተዳደሩ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ስለ ከተማዋ ሰላም፣ ልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ውይይት እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።
የታቀዱ ሥራዎችን ለማሳካትም የመንግሥት ሠራተኛው ሚናው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም በክልሉ ዕውቅና መሰጠቱን ጠቅሰዋል። በዚህም ከተማ አሥተዳደሩ በለውጥ ሂደት ላይ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም በ2017 በጀት ዓመት ያላለቁ የልማት ሥራዎችን ጨምሮ በፍጥነት እና በጥራት የመፈጸምን አስፈላጊነት አንስተዋል። በዝግጅት ምዕራፍ የተሠሩትን በመዳሰስ ለትግበራውም ዝግጅት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ አገልግሎት አሰጣጡን የማሳደግ አስፈላጊነትን አንስተዋል።
የሚሠሩ የልማት ሥራዎችም ባሕር ዳርን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው። ለዚህም የመንግሥት ሠራተኛው መተባበር እና ማስተባበር እንደሚጠበቅበት አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ጌታቸው ግዛቸው በከተማዋ የተረጋጋ ሰላም እየሰፈነ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም ሕዝቡ መሳተፉን ጠቅሰዋል።
ማኅበረሰቡ አካባቢውን ከመጠበቅ ጀምሮ እስከ ጸጥታ ኀይል ሥራ ድረስ ለሰላሙ በትኩረት መሠራቱን አንስተዋል።
ታጥቀው ጫካ ያሉ ወንድሞችን ወደ ሰላም እንዲመለሱ በማድረግ ሕዝቡ እየጠየቀ እና እየተሳተፈ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ሰላሙን አስተማማኝ ለማድረግ ከመንግሥት ሠራተኛው ጋርም ውይይቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ሰላሙን ለማስቀጠል ባለቤቱ ራሱ መኾኑን በመረዳዳት፣ አካባቢውን መጠበቅ እና ከመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ጋር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ወጋየሁ ሽመላሽ ሰላም ልማት እና መልካም አሥተዳደር የማይነጣጠሉ መኾናቸውን ጠቅሰው ለውጤታቸውም ሠራተኛው ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።
የሰላም ባለቤት ሕዝብ ነው፤ የባሕር ዳር ከተማን ሰላም እና ልማት ለማስፈን መንግሥት ሠራተኛውም እየሠራ ነው ብለዋል።
የእስካሁኑን የልማት እና የሰላም ሥራ ሠራተኛው እና ሕዝቡ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት። ማኅበረሰቡን የሚያማርሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችንም መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
መንግሥት ሕዝቡን በማሥተባበር ሰላሙን የማረጋገጥ እና ልማቱንም የማስቀጠል ኀላፊነት እንዳለበት አንስተዋል።
ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ብርሃን ሽፈራው የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በስፋት በመፈጸም ባለፈው በጀት ዓመት የነበረውን ስኬት ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ለልማት እንቅፋት የኾኑ ነገሮችን ምቹ ኹኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
