
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ኅዳር ሲታጠን” የሚለውን አባባል መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። የኅዳር መታጠን ለምን እንደኾነ እና ታሪካዊ ዳራውን እንዲኹም የጤና በረከቱን መረዳት ላይ ግን ቃሉን ደጋግሞ እንደመስማት እኩል አይደለም።
በሀገራችን ኅዳር መታጠን የጀመረበት ወቅት በጣም ረጅም መኾኑን ታሪክ ይናገራል።
“የኅዳር ሲታጠንን ታሪክ እና የጤና ጉዳይ አስመልክተው ከአሚኮ ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉት የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ስፔሻሊስት ሀኪሙ ዶክተር መኮንን አይችሉህም ዓለም በተለያዩ ጊዜያት በአስቸጋሪ ወረርሽኞች መመታቷን ከታሪክ አስቀድመዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንኳን እንደ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ሳርስ እና የመሳሰሉት ከባድ ወረርሽኞች በዓለም ደረጃ ብዙ ሀገራትን በማዳረስ አስጨናቂ ፈተናዎች ኾነው እንደነበር አስታውሰዋል።
ስለኅዳር ሲታጠን መነሻም ወቅቱ በኢትዮጵያ የዘመን ቀመር አቆጣጠር በ1911 ዓ.ም እንደነበር ነግረውናል። በወቅቱ ስፔን አካባቢ እንደመጣ የሚነገርለት ስፓኒሽ ፍሉ የተባለ ሳልን የሚያስከትል ከፍተኛ ትኩሳት ያለው የኢንፍሎይዛ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር ነው ያሉት።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአውሮፓ ለሚሊዮኖች ሕይዎት መቀጠፍ ምክንያትም እንደነበር ታሪኩን በማጣቀስ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም አንዷ የዓለም ክፍል እንደመኾኗ በ1911 ዓ.ም ተከስቶ የነበረውን የኢንፍሎይዛ ወረርሽኝ ለማባረር በየቦታው ቆሻሻን ሰብሰቦ ማቃጠል እንደ መፍትሄ ሲወሰድ እንደነበር ተናግረዋል።
በወቅቱ በዚሁ በሸታ እስከ 50 ሺህ ሰዎች የሞቱበት እንደነበረ ይታወሳል ብለዋል ዶክተሩ።
ወረርሽኙ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት እየተዛመተ በወቅቱ አልጋ ወራሽ የነበሩትን አጼ ኃይለ ሥላሴን ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎችም በበሽታው ተጠቅተው እንደነበር በታሪክ ማስረጃዎች ሰፍሯል ነው ያሉት።
ይህ ወረርሽኝ በስፋት በመስራጨት ከፍተኛ የሞት ቁጥር የታየበት፤ ባል እና ሚስትን ብቻን ያስቀረ፣ አባት የልጁን አስክሬን ብቻውን የቀበረበት እጅግ አስቃቂ ወረርሽን እንደነበር ነው የገለጹት።
ይህንንም ተከትሎ ሀኪሞቹ መፍትሄ ነው ያሉትን ያስቀመጡ ሲሆን ሕዝቡ ቆሻሻ ከቤቱ አውጥቶ እንዲያቃጥል ታዝዞ ነበር። የታሪኩን መነሻም ይሄ ነው።
በሽታው በቆሻሻ ምክንያት በፍጥነት እንደሚስፋፋ በአዋጅ መነገሩን እና እንዲጠፋም በጉዳዩ ዙሪያ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ቆሻሻዎች በሙሉ ከየሰፈሩ እየተለቀሙ ይቃጠሉ እንደነበርም ተናግረዋል።
ከጊዜ በኋላም አየሩ ስለታጠነ በሽታው እንደጠፋ ታምነበት። በየዓመቱ ኅዳር 12 በኅብረተሰቡ ዘንድ ቆሻሻን በማቃጠል “ኅዳር ሲታጠን” የሚል ስያሜ ተሰጠው ሲሉ ዶክተር መኮንን ገልጸዋል።
ይህ ክንውን አሁንም ቀጥሏል። የአካባቢያችንን ንጽሕና መጠበቅ እንዳለብን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሲባል በአንዳንድ አካባቢዎች ኅብረተሰቡም ቀኑን ጠብቆ ሲያከብረው ይስተዋላል ነው ያሉት ዶክተሩ።
ኅዳር ሲታጠን ከዚያ በኋላም እንደ አንድ የጤና ፖሊሲ ኾኖ እያገለገለ እንዳለ የሚናገሩት ዶክተር መኮንን ይህም በጎ ጎን ይዞ የመጣ ስለመኾኑ ገልጸዋል።
ያንን ጊዜ በማሰብ እና ኅዳር 12 በየአካባቢው ያለውን ቆሻሻ በማቃጠል”ኅዳር ሲታጠን” በሚል በሽታዎችን ከማስወጣት እና ከንጽሕና ጋር አስተሳስሮ እስካሁንም ይከበራል ነው ያሉት።
በመስከረም እና ጥቅምት ወር ጉንፋን መሰል ወረርሽኝ እና ሌሎች በሽታዎች በስፋት እንደሚስፋፉ የገለጹት ዶክተር መኮንን በእነዚህ ወራት ደግሞ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ስለሚሄዱ በሽታዎቹ የመተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ወቅቱ አበቦች የሚያብቡበት እና የሚፈኩበት ጊዜ በመኾኑ አለርጂ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚዛመት ጉንፋን በሰፊው ይሠራጫል ነው ያሉት።
ጉንፋን መሰል በሽታወችን ለመከላከል ደግሞ የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ እና ቆሻሻዎችን ሰብስቦ ማቃጠልም ከዚሁ ከኅዳር ወር ጋር በሚደረገው የጽዳት ዘመቻ ጎን ለጎን የሚሄድ ነው ሲሉ ዶክተሩ ተናግረዋል ።
ኅዳር ሲታጠን በጤና ፖሊሲው ረገድ ትልቅ አስተዋጾኦ እንዳለውም ዶክተር መኮንን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሐ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
