
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “የሕጻናት ጥበቃ እና የመጫወት መብት ለሁሉም ሕጻናት” በሚል መሪ መልዕክት በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው ዓለም አቀፍ የሕጻናት ቀን የመዝጊያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ ነው የተከበረው።
በባሕር ዳር ከተማም የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ከግሬስ የእናቶች እና ሕጻናት ማዕከል ጋር በመተባበር አክብረውታል።
የሕጻናትን መብቶች በተመለከተ መልዕክቶች የተላለፉ ሲኾን በሕጻናት የቀረቡ መዝሙሮች፣ የጥያቄ እና መልስ፣ የስፖርታዊ ውድድር እንዲሁም ውይይት ተካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ ሕጻናት የነገ ሀገር ተረካቢ እና ገንቢ ናቸው ብለዋል።
ሕጻናት ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነው፤ በዚህ ዙሪያም ግሬስ የእናቶች እና የሕጻናት ማዕከል ሰፊ ሥራ እያከናወነ ያለ ተቋም ነው ብለዋል ኀላፊዋ።
ሁሉም በኅብረት ሢሠራ የሚከብድ ነገር የለም፤ በጋራ መሥራት ለውጤት ያበቃል፤ ልጆችን መንከባከብ እና መርዳት የሁሉም ኅብረተሰብ ኅላፊነት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ልጆች ሁሉ እንክብካቤ እንደሚሹ በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ የቻለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሕጻናት መብት ደኅንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ ፈንታሁን መለሰ በዓሉ ከዚህ በፊት በስድስት ክፍለ ከተሞች ሲከበር መቆየቱን አንስተዋል።
ዛሬም እንደ ከተማ አሥተዳደር የማጠቃለያ መርሐ ግብር ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
በዓሉ ሲከበር የበርካታ ሕጻናትን ችግር ለመፍታት ታልሞ ስለመኾኑም አብራርተዋል። ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለልጆች ድጋፍ የማድረግ እና የሚገጥሟቸውን ችግሮች የመፍታት ሥራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል።
የመብት ጥሰት ተጋላጭ ሕጻናትን ለመጠበቅ ከውጭ ድርጂቶች ጋር በጋራ እየሠሩ ስለመኾኑም ተናግረዋል።
ረዳት የሌላቸው ልጆችን ተንከባክቦ ለማሳደግ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
