
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዱር ቤቴ – ቁንዝላ – ሻውራ – ፍንጅት- ገለጎ -ገንዳ ውኃ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በተገኙበት በ2013 ዓ.ም ነበር የተጀመረው።
የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ 261 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። በወቅቱ 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅም ተገልጿል። መንገዱን በ3 ዓመት ከ6 ወራት ለማጠናቀቅም ውል ተወስዷል።
መንገዱ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው። በአካባቢው በሥፋት የሚመረቱትን የግብርና ምርቶች በቀላሉ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማድረስ ፋይዳው የጎላ ነው።
ነገር ግን የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት እቅድ መሠረት ባለመጠናቀቁ ትልቅ ተስፋ ጥሎበት በነበረው ማኅበረሰብ በኩል ቅሬታን ፈጥሯል።
የቁንዝላ አካባቢ ነዋሪው ኢሳያስ ይትባረክ መንገዱ ለረጅም ጊዜ ሕዝቡ ሲጠይቀው የኖረ ጥያቄ መኾኑን ተናግረዋል። ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመገንባቱ እናቶች በወሊድ ወቅት ቶሎ ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ይህም እናቶችን ለሞት እንደሚዳርግ ነው የተናገሩት።
የመንገዱ ግንባታ መጀመር በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል። ፕሮጀክቱ እንዳይስተጓጎል ማኅበረሰቡ ሙሉ ኀላፊነቱን ወስዶ የጸጥታ ሁኔታውን እስከ ማስከበር የደረሰ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም አንስተዋል። ነገር ግን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመከናወኑ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ጌታቸው መሠረት የመንገድ ልማት ለአካባቢው ሕልውና መኾኑን ገልጸዋል። የመንገዱ መገንባትም ማኅበረሰቡ በጉጉት ሲጠብቀው የቆየ መኾኑን አንስተዋል።
በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቅቆ ችግራቸው ይፈታል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ገልጸዋል። ይህ ባለመኾኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ነው የገለጹት። መንገዱ በወቅቱ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ትኩረት እንዲሰጠውም ጠይቀዋል።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ዜድ ሲሲሲ (ZCCC) ዓለም አቀፍ ሥራ ተቋራጭ የሎት አንድ ኦፊስ ማናጀር አስቻለ ፈንቴ የፕሮጀክቱ ውል የተወሰደው አስቻይ ሁኔታዎችን መሠረት አድርጎ እንደነበር አንስተዋል።
ሥራ ከጀመረ ጀምሮ ግን በተያዘው ውል መሠረት ለማከናወን ሀገራዊ እና ክልላዊ የጸጥታ ችግሮች በመፈጠራቸው ዋነኛ እንቅፋት ኾነውብናል ነው ያሉት።
የግንባታ ቁሳቁስ ከውጭ ለማስገባት የዶላር እጥረት ችግር፣ ከሦሥተኛ ወገን ሙሉ በሙሉ ነጻ አለመደረግ፣ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ መናር ለፕሮጀክቱ መጓተት ተጨማሪ ተጽዕኖ የፈጠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የባሕር ዳር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ ጠቅላላ የመንገድ ፕሮጀክቱ በሦሥት ክፍሎች የሚከናወን መኾኑን ተናግረዋል። በሎት አንድ:- (ዱር ቤቴ ➔ ቁንዝላ ➔ ሻውራ ➔ ፍንጅት)፣ በሎት ሁለት:- (ፍንጅት ➔ገለጎ) እና በሎት ሦስት:- (ገለጎ ➔ገንዳ ውኃ) የሚከናወን መኾኑን አብራርተዋል።
ሎት አንድ 135 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም እና አጠቃላይ አፈጻጸሙ 36 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። 76 ኪሎ ሜትር የመሬት ቆረጣ፣ 38 ኪሎ ሜትር ሰብ ቤዝ እና 48 በመቶ ደግሞ የድሬኔጅ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
የሎት ሦስት ደግሞ 125 ኪሎ ሜትር እንደሚረዝም እና አፈጻጸሙም 32 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። ይህም 75 ኪሎ ሜትር የመሬት ቆረጣ እና ሙሌት፣ 24 ኪሎ ሜትር ሰብ ቤዝ እና 60 በመቶ ደግሞ የማፋሳሻ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። ሎት ሁለት ግን እስከ አሁን እንዳልተጀመረ አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቶቹ ቀድሞ በተያዘው ውል መሠረት መጠናቀቅ ሲገባቸው ከ4 ዓመታት በላይ ጊዜ ወስደው እንኳን ግማሽ ያክሉን ማከናወን አለመቻሉን ከአፈጻጸሙ መረዳት ይቻላል።
ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀጠለው የጸጥታ ችግር ለፕሮጀክቶቹ መጓተት ዋነኛ ምክንያቶች እንደኾኑ ኢንጅነር ዮሴፍ ወርቁ ተናግረዋል። የሥራ ተቋራጩ በሚፈለገው ደረጃ ሥራውን ለማከናወን ተጽዕኖ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በጸጥታ ችግሩ ስጋት ምክንያት ነዳጅ፣ ለመንገድ ሥራ የሚውል ፈንጅ እና ሌሎች ግብዓቶችን ለማቅረብ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን አመላክተዋል። የፕሮጀክቱ ጊዜ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የዋጋ ግሽበቱ እና አለመረጋጋቱ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩንም አንስተዋል።
የሥራ ተቋራጩ ያነሳው የዶላር እጥረት መኖሩን ያነሱት ኢንጂነሩ ለፕሮጀክቱ መጓተት ግን መሠረታዊ ችግር እንዳልኾነ አረጋግጠዋል። በውሉ መሠረት 85 በመቶ በብር በሚከፈለው አሠራር መሠረት ማሰኬድ እንደሚችል አብራርተዋል።
ከሦስተኛ ወገን ነጻ ለማድረግ የተወሰኑ ችግሮች እንዳሉ ጠቁመዋል። በአብዛኛው ማኅበረሰብ በኩል የጎላ ችግር እንዳላጋጠመም ገልጸዋል። ሥራ ተቋራጩ ነጻ በኾኑት አካባቢዎችም በሚገባ ማከናወን እንዳልቻለ ነው የገለጹት።
ማኅበረሰቡ በርካታ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል። የጸጥታው ጉዳይ ግን በአንድ አካባቢ ብቻ የሚወሰን ሳይኾን አጠቃላይ የግንባታ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ኮሪደር የሚወሰን ነው ብለዋል። ለዚህም የሁሉንም አካላት ትኩረት እንደሚፈልግም ነው የጠቆሙት።
መንገዱ እንዲጠናቀቅም ከሥራ ተቋራጩ ጋር ደብዳቤ እስከ መጻፍ የደረሰ ግፊት በማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ተናግረዋል። በተያዘው ኅዳር ወር አስፋልት የማንጠፍ ሥራ እንደሚጀመርም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
