
አዲስ አበባ: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ሀገራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያለመ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የግብርና ሚኒስትር አዲሡ አረጋ በግብርና ትራንስፎርሜሽን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የልማት አጀንዳችን ማዕከል ነው ብለዋል።
ትኩረታችን ግልጽ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የገቢ ጥገኝነትን በመቀነስ የመሬት እና የውኃ ሃብትን በአግባቡ እና በውጤታማነት መጠቀም ላይ ይሠራል ብለዋል።
የምርት ሥርዓትን በማዘመን ዘላቂ፣ ተወዳዳሪ እና ውጤታማ የምግብ ሥርዓትን መገንባት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
መስኖን ማስፋት፣ ሜካናይዜሽንን ማጠናከር፣ የክላስተር እርሻን ማሳደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዝርያን ማስተዋወቅ እና ሌሎችም በግብርናው ዘርፍ እየተሠራባቸው ያሉ ቁልፍ ጉዳዮች እንደኾኑም ተናግረዋል።
ግብርናን በማዘመን የኢትዮጵያንም ኾነ የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ከግብርና በላይ የክብር እና የኢኮኖሚ ነፃነት ጉዳይ በመኾኑ የተጋረጡ ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ ውሳኔ እና የአጋሮች ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሩሲያ በግብርናም ኾነ በሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርኪሂን ሩሲያ ለአፍሪካ ሀገራት በተለይም ለኢትዮጵያ ጠንካራ አጋር ናት ብለዋል። ይህ አጋርነትም የግብርናው ዘርፍ ትብብርን ያካተተ መኾኑንም ገልጸዋል።
ይህ አጋርነት የሚቀጥል መኾኑንም አረጋግጠዋል። የአፍሪካ ሀገራትን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ በዘርፉ ላሉ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት እና የአፍሪካን አርሶ አደሮች ብልጽግና ለማረጋገጥ በትብብር ይሠራል ብለዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ልዑክ መሪ ብሩስ ሎሬንዝ ቢበር በበኩላቸው የምግብ ሉዓላዊነት ለዜጎች አስቸኳይ እና መሠረታዊ ጉዳይ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ በተለይም ከሳህል ቀጣና እስከ አፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የምግብ ቀውስ መኖሩን ጠቅሰው በዚህም በአህጉሪቱ በአሁኑ ወቅት ከሩብ በላይ የሚኾነው ሕዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጠ መኾኑን ገልጸዋል።
ለዚህ የከፋ ችግር በዘርፉ መሪ የኾኑ አካላት አስቸኳይ ውሳኔ እና ትኩረት በመስጠት ተደራሽ ባልኾኑ አካባቢዎች ላይ ተገቢውን እርምት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
በዚህም ዓለም አቀፍ የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ጉባኤ ላይ የሩሲያ ተወካዮች፣ የአፍሪካ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ የቢዝነስ ሰዎች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎችም አካላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ መሠረት መቅጫ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
