
ደሴ: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን የሥራ ኀላፊዎች በቃሉ ወረዳ ደጋን ተገኝተው በዶሮ ርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን የዶሮ ርባታ ዘርፍን ጨምሮ በሌሎችም ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ላይ በተደረገው ድጋፍ እና ክትትል ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በተለይም በቃሉ ወረዳ ኢንተርፕራይዞችን በክላስተር በማደራጀት እየተከናወነ ያለው ተግባር ተሞክሮ የሚወሰድበት መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ከዶሮ ርባታ ዘርፍ በተጨማሪ በላም ርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ብለዋል።
የቃሉ ወረዳ ሥራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሬድዋን ሁሴን በወረዳው ወጣቶችን በክላስተር በማደራጀት በሥራ እድል ፈጠራ ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በተለይም በእንቁላል ጣይ ዶሮ ርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች በተደረገላቸው እገዛ ለውጥ ማስመዝገባቸውን አመላክተዋል። በወረዳው በሩብ ዓመቱ ለዘጠኝ መቶ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም ጠቅሰዋል።
በዶሮ ርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶችም ወረዳው ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ባመቻቸላቸው የሥራ እድል ተጠቃሚ መኾናቸውን ተናግረዋል። ከሚያረቧቸው የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች በቀን እስከ 17 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መኾናቸውም አንስተዋል።
ዘጋቢ:- ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
