የምርት ጥራትን በማረጋገጥ የሀገሪቱን ተወዳደሪነት ማሳደግ ይገባል።

2

አዲስ አበባ: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “ጥራት በተለየ እሳቤ እና ፈጠራ” በሚል መሪ ሀሳብ ከኅዳር 11/2018 ዓ.ም እስከ ኅዳር 14/2018 ዓ.ም የዓለም የምርት ጥራት ሳምንት በኢትዮጵያ ይከበራል።

በዓሉ በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።

በ1990ዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የጋራ ስምምነት በዓሉ መከበር የጀመረ ሲኾን ዓላማውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርት ጥራትን በተመለከተ ግንዛቤ ማስፋት ነው።

ጥራትን ለማረጋገጥ እና አምራቾች ምርቶቻቸውን በጥራት እንዲያመረቱ ተጠቃሚዎችም ጥራት ያላቸው ምርቶችን የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ ነው የጥራት ሳምንት የሚከበረው።

በሳምንቱም የኢትዮጵያ ተሰማሚነት እና ምዘና የጥራት ማረጋገጫ ያገኙ ከ100 በላይ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ያስተዋውቃሉ።

የኢትዮጵያ የተሰማሚነት ምዘና ድርጅት ዳይሬክተር ኢንጅነር መዓዛ አበራ በዓሉ
የምርት ጥራት ምን ማለት እንደኾነ የሚያግባባ ሃሳብ ላይ ለመድረስ ያግዛል ብለዋል።

አምራች እና ሻጮች ጥራት ያላቸው ምርቶችን ለኅብረተሰቡ በማቅረብ የኅብረተሰቡን ጤንነት እና ደኅንነት መጠበቅ እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ጥራትን ለማረጋገጥ ጥናት እና ምርምሮችን እንዲሁም የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት በየጊዜው ማሳደግ እና ማዘመን እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ሁሉን አቀፍ የአቅም ግንባታ ሥራ እና የጥራት ማስጠበቂያ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት መንግሥት ጥራትን ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎንፌ (ዶ.ር) መንግሥት ያለ ጥራት የሀገርን ኢኮኖሚ መገንባት እንደማይቻል በመረዳት የጥራት መንደር በመገንባት የምርቶችን ጥራት የማረጋገጥ ሥራ እየሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

በተለይም ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ በተሠራ ሥራ በ2017 ዓ.ም 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።

የምርት ጥራት በእያንዳንዱ ተቋማት አጀንዳ መኾን እንደሚገባውም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ለመገንባት ጥራት ያለው ምርት ወሳኝ መኾኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ሁሉም ድርጅቶች ጥራትን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች መሥራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጥራት ሳምንቱ ዐውደ ርዕይ ተሳታፊዎችም ለተጠቃሚው ጥራት ያላቸውን ምርቶች በማቅረብ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የጥራት ግብ ለማሳካት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ታሳቢ አድርገው ጥራት ላይ እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

ጥራትን ማረጋገጥ ሲባል የንግድ ስኬትን እና ዘላቂነትን፣ ፈጠራን እና ቅልጥፍናን ማሳደግ፣ ዘላቂ ልማት እና የኅብረተሰብ እሴት መፍጠር ማለት እንደኾነም አስገንዝበዋል።

በዓሉ የምርት ጥራትን ማረጋገጥ ብቻ ሳይኾን ዋነኛ ግቡ ውጤታማነትን በማጎልበት የሀገሪቱን ተወዳደሪነት ማሳደግ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሠላማዊት ነጋ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአራት የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጆችን አሻሽሎ ለማጽደቅ ከማኅበረሰቡ ጋር ምክክር እየተደረገ ነው።
Next articleየማሌዢያ ፌዴሬሽን ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ ቆይታ በተለያዩ ዘርፎች ስምምነት የተደረሰበት ፍሬያማ ቆይታ ነበር።