
ደሴ: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር በመተባበር መሻሻል በሚገባቸው የተለያዩ የገቢ ግብር አዋጆች ዙሪያ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በደሴ ከተማ መክሯል።
በምክክር መድረኩ አሚኮ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች መሻሻል በሚገባቸው አዋጆች ዙሪያ ግንዛቤ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት እፀገነት ታደሰ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው አዋጆች መሻሻል አለባቸው፤ ነጋዴውም በአቅሙ ልክ ሲከፍል ነው ሀገር የሚያድገው ብለዋል።
ከደቡብ ወሎ ዞን የጠበቆች ማኅበር የተወከሉት የሕግ ባለሙያው ሰለሞን ጎራው እና ከሂሳብ አዋቂዎች ማኅበር የተወከሉት ጋሻው አሰፋ ከዚህ በፊት የማያሠሩ አዋጆች ስለነበሩ እነሱን ማሻሻል ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መስፋፋት ምክንያት አዳዲስ የገቢ ማግኛ አማራጮችም እየሰፉ በመምጣታቸው አዋጆችን ማሻሻል ለኢኮኖሚው የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነውም ብለዋል።
በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ አሊ ይማም ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ገቢ ዕድገት በማሳየቱ እና ወቅታዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አዋጅ በማስፈለጉ የክልሉ መንግሥትም መሠብሠብ ያለበትን ገቢ እንዲሠበሥብ የገቢ ግብር አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል።
በምክር ቤት የሚወጡ አዋጆች ሕዝብንም መንግሥትንም የሚጠቅሙ መኾን ስላለባቸው ከመጽደቃቸው በፊት የተለያዩ አካላት እንዲሳተፉ እና ረቂቅ አዋጆቹ በሃሳብ እንዲዳብሩ መደረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የመድረኩ ዓላማ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግሉ እና አካታች አዋጆችን ለማውጣት አዋጆችን በውይይት ማዳበር በማስፈለጉ መኾኑን ገልጸዋል።
ዘመኑን የዋጁ እና አርዕስት የሌላቸው የገቢ አይነቶችን በአዋጅ ማካተት በማስፈለጉ ብሎም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያመነጨው ገቢ እያደገ ዘርፉም እየሰፋ በመምጣቱ ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።
አንዳንዶቹ አዋጆች ለረጅም ጊዜ ሳይሻሻሉ የቆዩ በመኾናቸው ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ ስለመገኘቱም አስረድተዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የንግድ ገቢ ግብር፣ የመሬት መጠቀሚያ እና እርሻ ግብር፣ የኤክሳይስ ታክስ እና የቴምብር ቀረጥ አዋጅ በአጠቃላይ አራት የገቢ ግብር ረቂቅ አዋጆችን አሻሽሎ ለማጽደቅ እየሠራ እንደሚገኝም ዶክተር መንገሻ ፈንታው ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ከድር አሊ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
