
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) “አገልጋይ እና የሰላም ዘብ፣ የመንግሥት ሠራተኛ ለሁለንተናዊ እምርታ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ የተሳተፉ የመንግሥት ሠራተኞችም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን ከተቋማት የሥራ ባሕሪ ጋር በማጣጣም በጥናት የተደገፈ እቅድ ማውጣት እና ተግባራዊነቱን በጠንካራ ክትትል ማረጋገጥ ላይ መሠራት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በብልሹ አሥራሮች ምክንያት ተገልጋዮች ለመልካም አሥተዳደር ችግሮች የሚዳረጉበትን አግባብ በቁርጠኝነት ታግሎ ማስተካከል እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማ ለማድረግ ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ማስፈን ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
የብልሹ አሠራር በሚፈፅሙ ሠራተኞች ላይ የተጠያቂነት አሠራር እየተተገበረ መኾኑን የጠቀሱት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰለሞን ጌታቸው በተለያዩ ተቋማት ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ሂደት ችግር የፈጠሩ ሠራተኞች በምርመራ ሂደት ውስጥ ያሉ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የመንግሥት የሥራ ሰዓትን በአግባቡ መጠቀም፣ ተገልጋይን ማርካት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ማሻሻል ከመንግሥት ሠራተኞች የሚጠበቅ ኀላፊነት መኾኑን አሳስበዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው በመንግሥት ተቋማት ኀላፊነትን አውቆ መሥራት ካልተቻለ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን መቅረፍ አይቻልም ብለዋል። በምንችለው ልክ እያገለገልን ነው ብሎ ራስን መጠየቅ እና የሚመጥን የአገልጋይነት ስብዕና መላበስ ይገባል ነው ያሉት።
ተቋማት ለማኅበረሰቡ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች ያለባቸውን ግዙፍ ኀላፊነት በመረዳት በዚሁ አግባብ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ:- በላይ ተስፋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
