የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በ2018 በጀት ዓመት 63 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

3

ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ ወቅታዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች፣ በሚያጋጥሙት ችግሮች እና መፍትሄዎች እንዲሁም መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እና በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኀላፊው በማብራሪያቸው የክልሉ መንግሥት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል፡፡ የክልሉ መሪዎች ክልሉን የማልማት ከፍተኛ ቁጭት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ በመኾኑም ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ ችግሮች የሚቀረፉበት እና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚኾንበት ፍኖተ ካርታ መተለሙን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የ25 ዓመቱ አሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል፡፡ የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም በ2018 በጀት ዓመት 63 በመቶ እና በ25 ዓመቱ መጨረሻ ደግሞ 85 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡

የክልሉ ምርት በ9 ነጥብ 5 በመቶ እንዲያድግ እና አምራች ኢንዱስትሪው 16 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

በበጀት ዓመቱ 607 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መዋዕለ ንዋይ ወደ ዘርፉ ለማምጣት ታቅዷል፡፡ ለዚህም በተመረጡ ዘርፎች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ተኪ ምርት ላይ ይተኮራል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ተኪ ምርቶች ተለይተዋል፡፡ ወደ ምርት የገቡም አሉ፡፡

ምርታማነት እና ቅልጥፍና፣ የተማረ የሰው ኀይል ልማት፣ ቴክኖሎጂ እና መዋቅራዊ ሽግግር የኢንዱስትሪው ምሰሶዎች መኾናቸውንም አቶ እንድሪስ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥትም ለዘርፉ ማደግ መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን አሻሽሏል፡፡ የባለሃብቶችን ውጣውረድ ለመቀነስም እየተሠራ ነው፡፡

የኀይል አቅርቦትን ጨምሮ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስ እና የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ከየተቋማቱ ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጫው የሥራ ዕድል መፍጠር እና ኢኮኖሚያዊ ስብራቱን ማከም ነው። በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 67 ሺህ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል። ለኢንዱስትሪው የሚመጥን የሰው ኀይል ማምረት እና ኢንዱስትሪዎችንም ለማብቃት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እና ማነቆዎችን በመፍታት ብቃት ያለው የሰው ኀይል ለመፍጠር ይሠራልም ነው ያሉት።

በክልሉ ብዙ ባለሃብቶች መሬት ይዘው ሳያለሙ የተቀመጡ የመኖራቸውን ያህል በተሻለ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ለማልማት የቀረቡ ስላሉ ማጣጣም ያስፈልጋል ነው ያሉት ኀላፊው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ቅድሚያ ለሚያለሙት ድጋፍ በማድረግ በማያለሙት ላይ እርምት መውሰዱ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይ 25 ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ እና ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪዎቹን ቁጥር ለማሳደግ እና የማምረት አቅማቸውን 85 በመቶ ለማድረስ እንደሚሠራም ጠቁመዋል፡፡

የመንግሥትን ጉድለት በመሙላት የክልሉን ኢኮኖሚ የሚያሸጋግሩ ይኾናሉ ብለዋል። ለዚህም 608 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ዕቅዱንም ትውልድ እየተቀባበለ እንደሚያሳካው ይጠበቃል፡፡

ከመንግሥት የሚጠበቀው ፍኖተ ካርታውን ማዘጋጀት እና ማስጀመር ነው፡፡ አጀማመሩም ጥሩ መኾኑን ጠቁመዋል። የሕዝብ ዕቅድ ስለኾነም ተባብሮ በመሥራት ዕቅዱን ማሳካት እንደሚገባም አቶ እንድሪስ አስገንዝበዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሥራ ፈላጊ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ኾነው ራሳቸውን እና ሌሎችን የሚጠቅሙ ወጣቶችን መፍጠር ይገባል።
Next articleአማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን በማጠናከር የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሠራ ነው።