
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አመልድ ኢትዮጵያ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሁለት ዓመታት በአማራ ክልል ሲተገበር የቆየውን የማያ ፕሮግራሞ አፈጻጸም ግምገማ ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የአመልድ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አለማየሁ ዋሴ (ዶ.ር) መድረኩ የተዘጋጀው አመልድ ኢትዮጵያ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየተገበረ ያለውን የማያ ፕሮግራም ባለፉት ሁለት ዓመታት ምን ውጤት እንዳመጣ ለመገምገም እና የተገኙ ትምህርቶችንም ለማየት ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በፕሮግራሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመለየት እና እንዴት ተሻሽሎ ውጤታማ ይኾናል የሚለውን ለመወያየት የተዘጋጀ መድረክ እንደኾነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሥራ እና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) መርሐ ግብሩ ከአማራ ክልል ውጭ በሌሎች ክልሎችም እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ራዕይ ያለው መርሐ ግብር ነው ያሉት ኀላፊው ለወጣቶች ተስፋ እና ራዕይ ኾኖ ወጣቶችን ለመጥቀም የሚሠራ ነው ብለዋል።
የመርሐ ግብሩ ራዕይ በአምስት ዓመት ውስጥ ወጣቶችን ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ መንግሥት ያልደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከአንድ ሚሊዮን በላይ መጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚኾኑት ሴቶች እንደኾኑም ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በመስጠት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
በክልሉ በአራት ማዕከላት በ23 ነጥብ 1ሚሊዮን ዶላር በላይ በኾነ ወጭ ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።
ለንብ ማነብ የኢንዱስትሪው መስፋፋት እንደ ሀገር የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያግዝ እንደኾነ እና አመልድ እና ማያ ፕሮግራም ለአማራ ሕዝብ ውጤታማ ሥራ እየሠሩ መኾኑንም አንስተዋል።
ወጣቶችም ዕድሉን በመጠቀም ሥራ ፈላጊ ሳይኾን ሥራ ፈጣሪ ኾነው ራሳቸውን እና ሌሎችን እንዲጠቅሙ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
