
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አዲሱን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመረቁበት ወቅት ለዲጂታል ኢትዮጰያ ጉዞ የተቋሙ አበርክቶ ትልቅ መኾኑን ተናግረው ነበር። ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ትኩረት ሰጥቶ በሠራቸው ሥራዎች በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን ማዳን እንዳስቻለም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ ከአሚኮ ዲጂታል ባደረጉት ቆይታ ኢንስቲትዩቱ ለሰው ሠራሽ አስተውሎት የምርምር እና ልማት ሥራዎች ወሳኝ ሚናን የሚጫወቱ 16 ፔታ ባይት የሚጠጋ መረጃ ማከማቸት የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የመረጃ ማከማቻ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) መዘርጋቱን ገልጸዋል። ይህ መሠረተ ልማት ግዙፍ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፕሮጀክቶች የሚፈልጉትን ፍጥነት እና አቅም ከፍ ለማድረግ ቁልፍ መኾኑን ተናግረዋል።
በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት አዳራሾች ተግባራዊ የተደረገው ድምጽን ወደ ጽሑፍ መቀየሪያ (ትራንስክሪፕሽን) ሥርዓት 96 በመቶ ትክክለኛ ውጤት በማስመዝገብ የፍትሕ ዘርፉን እያዘመነ መኾኑን ተናግረዋል።
ከአማርኛ በተጨማሪ አራት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን (አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ) የማሽን ቋንቋ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በመሠራቱ ድምጽን ወደ ጽሑፍ የመቀየር (ትራንስክሪፕሽን) እና የመተርጎም ሥራዎችን ማቅለሉንም ገልጸዋል።
ኮምፒውተሮች በመረጥነው ቋንቋ የተለያዪ ተገባራትን እንዲሠሩ ማድረግ ስንችል ያንን ቋንቋ የማሽን ቋንቋ አደረግን እንላለን ነው ያሉት።
ኢንስቲትዩቱ በጤናው ዘርፍም የዘመነ የቴክኖሎጂ ተግባራትን ማከናወኑንም ገልጸዋል።
ለአብነት የጡት ካንሰርን እና የተወሰኑ የሕጻናት የቆዳ በሽታዎችን የመለየት ሥራ የሚሠሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ውጤቶች በተመረጡ ሆስፒታሎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል። አይነት አንድ እና አይነት ሁለት የስኳር በሽታን ከመለየት አልፎ በቀጣዮቹ ዓመታት በበሽታው የመያዝ ዕድልን የሚተነብዩ ቴክኖሎጂዎች በተቋሙ መልማታቸውን እና ሥራ ላይ መኾናቸውንም ነግረውናል።
በቅርቡ ተዋውቆ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ታግዞ ወደ ሥራ እንዲመጣ እና የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ እንዲፋጠን የኢንስቲትዩቱ ሚና የላቀ መኾኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጄንስ ኢንስቲትዩት በሰው ኃይል ልማት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ተማሪዎችን እያሠለጠነ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ተቋሙ ሲመሠረት በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የአፍሪካ ቀዳሚ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ምርምር እና ልማት ልኅቀት ማዕከል የመኾን ራዕይን ሰንቆ መነሳቱን ገልጸዋል። “እኛ ያለፍንበት ፈተና ለሌሎች የአፍሪካ እህት ወንድሞቻችን ልምድ ኾኖ ያገለግላል” በማለት ከሀገር የተሻገረ በጎ እሳቤ ያለው ተቋም መኾኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በዲጂታላይዜሽን እና በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ በአምስት ዓመታት ብቻ የሚታይ ለውጥ ያመጣ ተቋም እንደኾነ በጥቂቱ የጠቃቀስናቸው ሥራዎቹ ምሥክር ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
