
ባሕር ዳር: ኅዳር 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ለፖሊስ መሪዎች እና አባላት የሪፎርም አፈጻጸም እና የመሪዎች አቅም ግንባታ ሥልጠና እየሰጠ ነው።
በሥልጠናው ማስጀመሪያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የክልሉ የፖሊስ ኀይል ክልሉ በገጠሙት ተደጋጋሚ ችግሮች ሀገራዊ እና ክልላዊ ተልዕኮውን በሚገባ መወጣት የቻለ ነው ብለዋል።
በውስጥም በውጭም የሀገሪቱ ጠላቶች ብዙ ፍላጎት አላቸው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በየጊዜው የሚያጋጥሙ ፈተናዎችንም በጽናት መሻገር እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም የፖሊስ ሠራዊቱ ውስጣዊ አንድነቱን ያጠናከረ፣ ለዓላማ የቆመ፣ የሀገሪቱን መጻኢ እጣ ፈንታ በውል የተረዳ፣ በሥነ ልቦና የተዘጋጀ ኀይል ኾኖ መቆም ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ሥልጠናው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታውን በሚገባ በመረዳት የተቀራረበ ግንዛቤ እና አመለካከት በመያዝ ለሀገር እና ለሕዝብ ኀላፊነት ለመውሰድ የሚያስችል መኾኑንም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው እየተሰጠ የሚገኘው የአቅም ግንባታ ሥልጠና በተቋሙ የተከናወነውን ሪፎርም ተግባራዊ ለማድረግ መኾኑን ጠቁመዋል።
ዓለም የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በመገንዘብ ጊዜው የሚጠይቀው የፖሊስ መሪ ለመፍጠር ያለመ እንደኾነም ገልጸዋል።
የፖሊስ ተቋሙ ከተለመደው አሠራር በመውጣት ከጊዜው ጋር አብሮ እንዲራመድ ዘመናዊ የፖሊስ አሠራሮችን ለመተግበር የሚያስችል የለውጥ ማስጀመሪያ ነው ብለዋል። የተደረገው ሪፎርም ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ከሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል ነው ያሉት።
ፖሊስ ዋና ሥራው ሰብዓዊ መብትን ማክበር እና ማስከበር ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ሪፎርሙም የዜጎችን መብት እና ክብር በሚያከብር መልኩ የፖሊስን ተግባር ለማከናወን እንደሚያሰገድድም አስገንዝበዋል።
ሪፎርሙ በሰነድ ላይ የሚቀመጥ ጽሑፍ ሳይኾን በተግባር የምንኖረው ነው ብለዋል። ለውጥ የሚጀምረው ከግለሰብ መኾኑንም ጠቁመዋል። ይህንን በመገንዘብ የፖሊስ መሪዎች አርዓያ በመኾን የተከታዮቻቸውን አቅም በመገንባት፣ በማበረታታት እና በማሳደግ አጠቃላይ የተቋሙን ብቃት ማሳደግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ሠልጣኞች በሥልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀት በቅንነት እና በቁርጠኝነት ወደ ተግባር በመለወጥ የለውጥ አርዓያ መኾን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
